የሀገር ውስጥ ዜና

ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ሲያዘዋውሩ የተያዙ ግለሰቦች በእስራት ተቀጡ

By Adimasu Aragawu

February 23, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችን ለጽንፈኛው ቡድን ለማቀበል ሲያዘዋውሩ የተያዙ ግለሰቦች ጽኑ እስራት እና የገንዘብ ቅጣት ተላልፎባቸዋል።

የቅጣት ውሳኔ የተላለፈባቸው ተከሳሾቹ 9 ፒኬኤም የተባለ መትረየስ የጦር መሳሪያ በሕገ ወጥ መንገድ በተሽከርካሪው አካል ውስጥ በመደበቅ በማጓጓዝ ላይ እያሉ ከመነሻው ከጋምቤላ ክልል ጀምሮ በተደረገ ክትትል ነበር በቁጥጥር ስር የዋሉት።

ተከሳሾቹ 1ኛ ኃይሉ ደሳለኝ፣ 2ኛ ምናለ አለነ፣ 3ኛ አለነ ተፈሪ እና 4ኛ ደጉ ባዩ በመከላከያ ሠራዊት፣ በብሔራዊ መረጃና ደህንነት እና በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የፀጥታ አካላት ክትትል በፍቼ ከተማ በቁጥጥር ስር የዋሉ መሆናቸው ተመላክቷል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ዐቃቤ ሕግ ጽ/ቤት ተከሳሾቹ ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ሲያዘዋውሩ በየካቲት 12 ቀን 2018 ዓ.ም ከነተሽከርካሪው እጅ ከፍንጅ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቅሶ÷ የጦር መሳሪያ አዋጅ ቁጥር 1177/2012 አንቀጽ 4 እና አንቀጽ 22 ስር የተመለከቱ ድንጋጌ መተላለፍ የሚል ዝርዝር ክስ አቅርቧል።

ተከሳሾቹ እጅ ከፍንጅ የተያዙ መሆናቸውን ተከትሎ በክስ ዝርዝሩ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት መፈጸማቸውን በማመን ቃላቸውን የሰጡ ሲሆን÷ ፍርድ ቤቱ የአቃቤ ሕግ ማስረጃ መስማት ሳያስፈልገው በወንጀል ሕግ አንቀጽ 134 ንዑስ ቁጥር 1 መሰረት የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።

በዚህም በተሻሻለው የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 3/2017 መሠረት ተከሳሾቹን እያንዳንዳቸውን በ12 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል።

በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾችን በ50 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ እንዲሁም 4ኛ ተከሳሽ የ20 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኗል።

በታሪክ አዱኛ