አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የድህረ ክፍያ ተጠቃሚ ደንበኞች ባሉበት ቦታ ሆነው የፍጆታ ሂሳባቸውን ማወቅ የሚችሉበትን አሰራር በሙከራ ደረጃ አስጀምሯል፡፡
የተቋሙ የኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ አንዋር አብራር ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት÷ የተጀመረው አሰራር ከድህረ ክፍያ ተጠቃሚ ደንበኞች የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመቅረፍ ያስችላል፡፡
ከደንበኞች የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት ደንበኞቹ ባሉበት ሆነው የእጅ ስልካቸውን በመጠቀም የቆጣሪ ንባባቸውን የሚያስገቡበት የቴሌግራም ቻትቦት የሙከራ ትግበራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
የሙከራ ትግበራው ከ16 ሺህ በላይ የድህረ ክፍያ ተጠቃሚ ደንበኞች ባሉበት የሰሜን አዲስ አበባ ሪጅን ቁጥር አራት የአገልግሎት መስጫ ማዕከል ላይ ብቻ ተጀምሯል ነው ያሉት፡፡
በዚህም ከየካቲት 13 ቀን እስከ የካቲት 23 ቀን 2018 ዓ.ም ደንበኞች የፍጆታ ንባባቸውን በቀላሉ በቤታቸው ሆነው በ @eeuchatbot ለተቋሙ እንዲልኩ ጥሪ መቅረቡን ጠቁመዋል፡፡
የዲጂታል አሰራሩ ለደንበኞች በቀላሉ ተደራሽ ለመሆን፣ የፍጆታ ሂሳብን በወቅቱ ለመፈጸም፣ ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት እንዲሁም ጊዜና ወጪን ለመቆጠብ ያስችላል ብለዋል፡፡
በሙከራ ደረጃ የተጀመረው አሰራር ያሉበትን ክፍተቶች እና ጥንካሬዎች በመለየት በቀጣይ በሌሎች ሪጅኖች እና የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት ለማስፋት መታቀዱንም ገልጸዋል፡፡
በመሳፍንት እያዩ