ቢዝነስ

በመዲናዋ ቅዳሜና እሑድ ገበያዎች የምርት እጥረት እንዳያጋጥም…

By Yonas Getnet

February 23, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ቅዳሜ እና እሑድ ገበያዎች የምርት እጥረት እንዳያጋጥም በቅንጅት እየተሰራ ነው አለ የከተማ አስተዳደሩ ሕብረት ሥራ ኮሚሽን።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ሽታዬ መሀመድ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በከተማዋ የፍጆታ ምርቶች እጥረት እንዳያጋጥም ከክልሎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል።

በተለይም የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል ሕብረተሰቡ በቅዳሜ እና እሑድ ገበያዎች በቂ ምርት ማግኘት እንዲችል በትብብር እየተሰራ መሆኑን ገልጸው ÷ ምርቶች ለተጠቃሚዎች በአግባቡ እንዲደርሱ የተቀናጀ ሥራ መሰራቱን ጠቁመዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ከሸማቾች ሕብረት ስራ ማሕበራት ጋር በመተባበር የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ 325 ሚሊየን ብር ድጎማ ማድረጉን ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ የተለያዩ የማሕበረሰብ ክፍሎች በማሕበር ተደራጅተው እንዲንቀሳቀሱ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው÷ በዚህም ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።

እንዲሁም ማሕበራት የሚሰጧቸውን አገልግሎት ለመከታተል የሚያስችሉ የማዘመን ስራዎች ተሰርተዋል ያሉት ኮሚሽነሯ÷ ኦዲት የማድረግ ሥራዎች እንደሚሰሩ አመልክተዋል።

በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት 149 ማሕበራት መደራጀታቸውንና እነዚህም ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ከማድረግ አንጻር ትልቅ ሚና እንደሚኖራቸው አስረድተዋል።

ኮሚሽኑ ባከናወናቸው የሪፎርም ስራዎች ሕብረት ስራ ማሕበራት ከሸማችነት ወደ አምራችነት እንዲሸጋገሩና እሴት እንዲጨምሩ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው÷ የከተማዋ ነዋሪዎች ከማሕበራት በመግዛት እንዲጠቀሙ አስገንዝበዋል።

በዮናስ ጌትነት