አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊ እና ገለልተኛ እንዲሆን የድርሻችንን እንወጣለን አሉ የጨፌ ኦሮሚያ አባላት፡፡
አስተያየታቸውን ለፋና ዲጂታል የሰጡት የጨፌው አባላት÷ የዘንድሮው ምርጫ ፍትሃዊ፣ ተዓማኒና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ለማስቻል ለሕብረተሰቡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እየሰሩ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
ሕብረተሰቡ በሰላማዊ መንገድ ለፈለገው የፖለቲካ ፓርቲ ድምጹን እንዲሰጥና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሐሳባቸውንና ፕሮግራማቸውን በነጻነት እንዲያስተዋውቁ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል፡፡
ፓርቲዎች በማሕበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለውን አሸናፊ ሐሳብ በመያዝ መቅረብ እንደሚጠበቅባቸውም አጽንዖት ሰጥተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የምርጫ ሂደት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ያነሱት የጨፌ አባላት÷ በዘንድሮው ምርጫ የዕጩዎች ምዝገባ በዲጂታል አማራጭ መሆኑ የምርጫውን ተዓማኒነት እንደሚያሳድግ ተናግረዋል፡፡
ሕብረተሰቡም የምርጫ ካርዱን በመውሰድ ድምጹን ለፈቀደው የፖለቲካ ፓርቲ ለመስጠት መዘጋጀት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
በሲፈን መገርሳ