አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከበጋ መስኖ ከ15 ነጥብ 6 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ተሰብስቧል አለ የክልሉ ግብርና ቢሮ።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ኡስማን ሱሩር ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ የግብርናን ምርት እና ምርታማነት በማሳደግ የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሰፊ የንቅናቄ ስራዎች እየተሰሩ ነው።
በክልሉ እየተከናወነ በሚገኘው የበጋ መስኖ ልማት የአካባቢዎችን ጸጋ በመለየትና በማልማት ሕብረተሰቡን ያሳተፈ ንቅናቄ በማካሄድ ወደ ተግባር መገባቱን አንስተዋል።
በዚህም በሁለት ምዕራፍ 148 ሺህ ሄክታር ማሳ በማልማት ከ37 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ጠቁመዋል።
በመጀመሪያው ምዕራፍ የበጋ መስኖ ከ126 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሰብል እንዲሸፈን መደረጉን አንስተው÷ እስካሁን ከ54 ሺህ ሄክታር መሬት 15 ነጥብ 6 ሚሊየን ኩንታል ምርት መሰብሰቡን ተናግረዋል።
የመስኖ ልማት ስራ በሕብረተሰቡ ዘንድ የነበረውን አመለካከት በመቀየር የስራ ባሕል ለውጥ እያመጣ እንደሚገኝ ገልጸው÷ ይህም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተቀመጡ ግቦች በውጤት እንዲታጀቡ ያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም የጸደይ ወቅትን እንደ አንድ የምርት ወቅት በመውሰድ በትንሽ እርጥበት ቶሎ የሚደርሱ የሰብል ዓይነቶችን በመዝራት ተጨባጭ ውጤት የማምጣቱ ስራ በከፍተኛ ደረጃ እያደግ እንደሚገኝ አንስተዋል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት የማይታረሰውን መሬት ወደ ልማት በማስገባት አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ የስራ ዕድል እንዲፈጠር እና ለሀገር ኢኮኖሚ አስተዋጽዖ እንዲያበረክት የሚያስችል ስራ መሰራቱንም ጠቁመዋል።
የምዕራፍ ሁለት የበጋ መስኖ እርሻ ለመጀመር እየተሰራ መሆኑንም አቶ ኡስማን ገልጸዋል።
በዮናስ ጌትነት