አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ስርዓትን የሚያዘምን ዲጂታል አሰራር ይፋ አድርጓል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ በማስተዋወቂያ መድረኩ ላይ እንዳሉት÷ የዲጂታል ስርዓቱ በኢትዮጵያ በእያንዳንዱ ወረዳ ምን አይነት የጤና ችግር አለ የሚለውን ለመለየት ያስችላል።
ስርዓቱ በፊት የነበረውን የተበታተነ የመረጃ አያያዝ የሚያስቀር መሆኑን ገልጸው÷ ይህም በየደረጃው የጤና መረጃ ልውውጥ እንዲሳለጥ ያግዛል ብለዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዳይሬክተር ዶ/ር መልካሙ አብጤ በበኩላቸው÷ ዲጂታል ስርዓቱ የጤና አደጋዎችን በተቀናጀ መልኩ ለመቆጣጠር እንደሚያግዝ አንስተዋል።
ተቋሙ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር የልህቀት ማዕከል ለመሆን እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው÷ ዲጂታል ስርዓቱ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ርምጃዎችን ለመውሰድና የተቀናጀ የክትትል ስራ ለመስራት እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።
ዲጂታል ስርዓቱ ትንተናዎችን ለመስራት፣ ጊዜ ለመቆጠብና የታካሚዎችን መረጃ በአግባቡ ለማስቀመጥ ይረዳልም ነው ያሉት፡፡
በመርሐ ግብሩ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን÷ በአዲስ መልክ የተደራጀው የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ማስተባበሪያ ማዕከል ተመርቋል።
እንዲሁም ኢንስቲትዩቱ የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ስርዓትን ለማጠናከር የሚውሉ የመረጃና ግንኙነት ቴክኖሎጂ ግብዓቶችን አስረክቧል።
በየሻምበል ምህረት