የሀገር ውስጥ ዜና

በአማራ ክልል ከተሞች ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ልማቶች…

By Mikias Ayele

February 25, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል ከ700 ከተሞች በላይ በመዋቅራዊ ፕላን እየተመሩ ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ልማቶች እየተሰሩ ነው አለ የክልሉ ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ፡፡

የቢሮው ኃላፊ ሞላ መልካሙ (ዶ/ር) በክልሉ በሪጆፖሊታን፣ በመካከለኛ ከተማ፣ አነስተኛ ከተሞች፣ መሪ ማዘጋጃ፣ ንዑስ ማዘጋጃ እና ታዳጊ ከተማ ደረጃ የሚገኙ 729 ከተሞች መኖራቸውን ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡

ከአጠቃላይ ከተሞች 90 በመቶ የሚሆኑት መዋቅራዊ ፕላን የተሰራላቸው መሆናቸውን ጠቅሰው÷ በክልል ደረጃ የፕላን ኢንስትቲዩት ከተሞች ፕላናቸውን እንዲተገብሩ ቁጥጥር በማድረግ ልማቱ መዋቅራዊ ፕላኑን ተከተሎ እየተፋጠነ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

በክልሉ በሚገኙ ከተሞች የፕላን ጥሰት ሲደረግ በህግ አግባብ እንዲስተካከል እየተደረገ መሆኑን ገልጸው÷ የፕላን ዘመን ባለቀባቸው ከተሞች የመዋቅራዊ ፕላን ክለሳ ፕሮግራም እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

መዋቅራዊ ፕላኑ የከተሞች ወቅታዊ ልማት ከከተሞች ዘላቂ እድገት ጋር እየተሻሻለ እንዲሄድ ለማድረግና በሁሉም የክልሉ ከተሞች ተግባራዊ እንዲደረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በክልሉ የከተሞች እድገት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን አንስተው÷ ከተሞች ያላቸውን የተፈጥሮ ሀብት እና የመልማት ፀጋ ከግምት በማስገባት ፕላን እየወጣላቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በከተሞች የአረንጓዴ ልማት፣ የቤት አቅርቦት፣ ደረጃውን የጠበቀ ዘላቂ መሰረት ልማት፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እና መልካም አስተዳደርን በማስፈን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ እየተሰራ መሆኑንም ኃላፊው አመላክተዋል፡፡

በተጨማሪም ከተሞችን ውብና ማራኪ ለማድረግ እንደ ሀገር የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ስራዎችን የመተግበር ስራዎች በተመረጡ ከተሞች እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በሚኪያስ አየለ