የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያን እምቅ የቱሪዝም ጸጋዎች በመጠቀም የብልጽግና ጉዞን ማፋጠን ይገባል – አቶ ጥላሁን ከበደ

By Adimasu Aragawu

February 26, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ኢትዮጵያ ያሏትን ታሪክ፣ ባህል፣ ተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም ጸጋዎችን በመጠቀም የብልጽግና ጉዞዋን ማፋጠን ይገባል አሉ።

ሀገራዊ የቱሪዝም ዘርፍ የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በአርባምንጭ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለቱሪዝም ዘርፍ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዩኔስኮ የተመዘገቡ የክልሉን የቱሪዝም ሃብቶች በፌደራሊዝም ስርዓት ውስጥ ከሌሎች ክልሎች ጋር በማቀናጀት ዘርፉን የኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን አስረድተዋል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ በበኩላቸው÷ ባለፉት ስድስት ወራት በገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች አዳዲስ መዳረሻዎችን በማልማትና የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን በማነቃቃት አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በዓለም ፈጣን የቱሪዝም እድገት ካስመዘገቡ ሀገራት ተርታ መሰለፏን አንስተው÷ አዲስ አበባ የዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ማዕከል መሆን መቻሏንም አመልክተዋል።

ይሁን እንጂ በአገልግሎት አሰጣጥና በመዳረሻዎች አያያዝ ላይ የሚታዩ የጥራት ክፍተቶች አሁንም ተግዳሮት መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በቀጣይ ስድስት ወራት የአገልግሎት ልህቀትን ለማረጋገጥና ዘርፉን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማዘመን በትኩረት እንደሚሰራ ማረጋገጣቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ለፋና ዲጂታል ገልጿል።