አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመራጮች እና ዕጩዎች የዲጂታል ምዝገባ ሥርዓት ለምርጫ ተአማኒነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል አሉ ምሁራን።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የመራጮችና የዕጩዎች የዲጂታል ምዝገባ ሥርዓትን በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሒደት ላይ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሙሉጌታ አያሌው (ዶ/ር) ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት ÷ አዲሱ የዲጂታል ምዝገባ ሥርዓት ለወደፊት ምርጫዎች ተአማኒነት ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡
መረጃው ያለምንም መዛባትና ትክክለኛነቱ ተጠብቆ መድረስ እንዳለበት ገልጸው÷ ቴክኖሎጂ ምርጫን ለማሳለጥ ያለውን ሚና በመረዳት አጠቃቀሙ ላይ በቂ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑት ሙሉዓለም ኃይለማርያም በበኩላቸው÷ ምርጫ ቦርድ የዕጩዎች እና የመራጮች ምዝገባን በዲጂታል ሥርዓት መደገፉ ጊዜና ገንዘብን ለመቆጠብ ያስችላል ብለዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ዴሞክራሲያዊ መብትን በአግባቡ ለመጠቀም እና የመረጃ አያያዝ ችግርን ለመፍታት አስቻይ ሁኔታ እንደሚፈጥር ነው የተናገሩት፡፡
ሒደቱን ግልጽና ቀልጣፋ ከማድረግ አኳያ ጉልህ ሚና እንዳለው እና የምርጫውን ግልጸኝነት ለማሻሻል እንዲሁም ሰላማዊ የምርጫ ተሳትፎን ለማጠናከር ከፍተኛ እገዛ እንዳለው አብራርተዋል፡፡
የዲጂታል ምዝገባ ሥርዓቱ የሥራ ቅልጥፍናን ለማሻሻል እና የመረጃ ትክክለኛነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም ወጪን በመቀነስ የቦርዱን ተቋማዊ አቅም ያጠናክራል ያሉት ደግሞ የምርጫ ቦርድ የክልል ቅ/ጽ ቤቶች ማስተባበሪያ ክፍል ኃላፊ ቀነኒ እንሰርሙ ናቸው።
የዲጂታል ሥርዓቱ ሶስት የምዝገባ አማራጮችን እንደሚያካትት ጠቁመው÷ እነዚሀም “ምርጫዬ” በተሰኘ የሞባይል መተግበሪያ፣ በገጸ ድር እና በምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት በታብሌት መመዝገብ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
በሌላ በኩል የዲጂታል ምዝገባ ሥርዓቱ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ምቹ ሆኖ መዘጋጀቱን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በሲፈን መኮንን