የሀገር ውስጥ ዜና

መገናኛ ብዙኃን የሀገራዊ ምክክሩን ዐውድ መሠረት አድርገው እንዲዘግቡ ተጠየቀ

By Adimasu Aragawu

February 26, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መገናኛ ብዙኃን የሀገራዊ ምክክሩን ዐውድ መሠረት አድርገው እንዲዘግቡ ጥሪ አቀረበ፡፡

ኮሚሽኑ ከመገናኛ ብዙኃን ተቋማት አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር በቀጣይ የኮሚሽኑ ሥራዎችና የመገናኛ ብዙኃን ተሳትፎ ዙሪያ ውይይት አካሂዷል፡፡

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር በዚህ ወቅት÷ ሚዲያዎች የኮሚሽኑን ሥራዎች ለሕዝብ ከማድረስ ረገድ ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሲወጡ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡

በቀጣይም መገናኛ ብዙኃን የሀገራዊ ምክክሩን ሒደት ሃላፊነት በተሞላበት መልኩ በስፋት እንዲዘግቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ለተሳታፊዎች የምክክር ዘገባ መርሆችን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም የሀገራዊ ምክክሩን አጠቃላይ ዐውድ መሠረት በማድረግ ዘገባ መሥራት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

መገናኛ ብዙኃን አካታችነትን፣ ወካይነትን፣ ግልጽነትን፣ መረጃን ማዋሃድና ማቀናበርን በሥራዎቻቸው ላይ በማካተት ማሕበረሰቡ በሀገራዊ ምክክር ሒደቱ ላይ የተሟላ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም አንስተዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የኮሚሽኑ የአራት ዓመታት አፈጻጸም፣ ቀጣይ ዕቅዶች እና ከመገናኛ ብዙኃን ጋር የተከናወኑ የአጋርነት ተግባራት በኮሚሽኑ ባለሙያዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡