አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ምርት እና ምርታማነትን እየጨመረ መጥቷል አለ የክልሉ ግብርና ቢሮ።
በቢሮው የተፈጥሮ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብዱልከሪም ሙሳ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በክልሉ 22 ወረዳዎች በርካታ የማሕበረሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እየተከናወነ ይገኛል።
ስራውን ከ57 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ለማከናወን ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸው÷ በየዓመቱ በተሰራው ስራም በጎርፍ እየተሸረሸረ የሚሄደውን ለም አፈር እንዲቆም በማድረግ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
ገላጣማ የነበሩ አካባቢዎች በተሰራው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ አሁን ላይ ምርት መስጠት መቻላቸውን ጠቅሰው÷ ስራው ዘላቂ በሆነ መንገድ እንዲቀጥል የክትትልና ድጋፍ ስራዎች እንደሚከናወኑ አስረድተዋል።
ዜጎች በየአካባቢያቸው በዘላቂነት የተሰሩ ስራዎችን እንዲንከባከቡ ለማስቻል በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል በቀጣይ ክረምት ለሚደረገው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረገ መሆኑን ገልጸው÷ በዚህም ወደ 60 ሚሊየን የሚጠጋ ችግኝ ለመትከል መታቀዱን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ እየሰራች የምትገኘው የአፈር እና ውሃ ጥበቃ እንዲሁም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ስራዎች ከኢትዮጵያ አልፎ በዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ላይ በጎ ተጽዕኖ መፍጠር የሚያስችል መሆኑንም አመልክተዋል።
በዮናስ ጌትነት