አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል ዘመናዊ የእንስሳት እርባታ ስራ ተጨባጭ ውጤት አስገኝቷል አለ የክልሉ እንስሳትና ዓሣ ሃብት ልማት ቢሮ።
ቢሮው በክልሉ ሰሜን ሸዋ ዞን አንጎለላና ጠራ ወረዳ በዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን ከተለያዩ የሚዲያ ባለሙያዎች ጋር በዛሬው ዕለት ምልከታ አድርጓል።
የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሀብታሙ ሁነኛው በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ በክልሉ የእንስሳት ሀብትን ለማልማት በዝርያ ማሻሻል፣ እንስሳት ጤና ጥበቃ እና መኖ ልማት ላይ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል።
በክልሉ በወተት ልማት፣ እንስሳት ማድለብ፣ ዶሮ እርባታ፣ ንብ ማነብ እና ዓሣ ሃብት ልማት ላይ ትኩረት በመስጠት ሙያዊ ሥልጠና በመስጠት፣ ቴክኖሎጂና ግብዓት አቅርቦትን በማሟላት እንዲሁም ሙያዊ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ለዘርፉ ውጤታማነት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
በዘርፉ በግል፣ በማሕበርና በኢንቨስትመንት ደረጃ የተከናወኑ የእንስሳት ሃብት ልማት ስራዎች ተጨባጭ ውጤቶች ማስገኘታቸውንም ተናግረዋል።
አርሶ አደሮችና የከተማ ነዋሪዎች እንቁላል፣ ወተት እና ማር እንዲያመርቱ በማድረግ የተመጣጠነ ምግብ ተጠቃሚነትን ማሳደግ መቻሉን ጠቁመዋል።
በሰላም አሰፋ