የሀገር ውስጥ ዜና

እያደገ የመጣው የኢትዮ- አዘርባጃን ሁለንተናዊ ትብብር…

By Melaku Gedif

February 27, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በፈረንጆቹ 1992 የተጀመረው የኢትዮጵያ እና አዘርባጃን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አሁን ላይ አዲስ ምዕራፍ ላይ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያና አዘርባጃን በተለያዩ ዘርፎች ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ ለማሳደግ በትብብር ሲሰሩ የቆዩ ሲሆን ÷ በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሀገራቱ ትስስር ይበልጥ እየተጠናከረ መጥቷል።

ሁለቱ ሀገራት በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በግብርና፣ በቴክኖሎጂ፣ በፍትሕ፣ በጸጥታና ደኅንነት እንዲሁም ሌሎች ዘርፎች ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር የተለያዩ ስምምነቶችን ተፈራርመዋል፡፡

የተደረሱ ስምምነቶችን ተግባራዊ ለማድረግ እና ለማሳለጥም የሀገራቱ ከፍተኛ አመራሮች በተለያዩ ጊዜያት በመገናኘት መምከራቸው ይታወሳል፡፡

በኢትዮጵያና አዘርባጃን መካከል በመደበኛነት የሚካሄደው የፖለቲካ ምክክርም ሀገራቱ ያላቸውን ሁለንተናዊ ግንኙነት ማለትም በግብርና፣ ማዕድን፣ ማኑፋክቸሪንግ እና አረንጓዴ ኢኮኖሚ ዘርፎች የበለጠ እንዲጠናከር አግዟል፡፡

ሀገራቱ በእንስሳትና ሰብል ልማት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እርሻ፣ በውሃና መሬት አጠቃቀም፣ በዲጂታል ግብርና፣ በቴክኖሎጂ አተገባበር፣ በግብርና ምርቶች ግብይት፣ በመስኖና ሌሎች የግብርና ልማት መስኮች በጋራ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

ኢትዮጵያ ወደ አዘርባጃን ከምትልካቸው ምርቶች መካከል ሰሊጥ፣ የተቆላ ቡና፣ ተልባ፣ የፍየል እና የበግ ሥጋን ጨምሮ ሌሎች ምርቶች ይገኙበታል፡፡

በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ከአዘርባጃን በከፊል የተጠናቀቁ የብረት እና የቆርቆሮ፣ የሴንትሪፉጅ አካላት እና የኤሌክትሪክ ሰርኪዩቶችን የሚከላከሉ መሳሪያዎችን ታስገባለች፡፡

ከቴክኖሎጂ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያና አዘርባጃን በሰው ሰራሽ አስተውሎትና ሌሎች ዘርፎች በትብብር በመስራት ላይ ናቸው፡፡

አዘርባጃን በኤሌክትሮኒክ አገልግሎቶች ዲጂታይዜሽን ላይ ለኢትዮጵያ ልምዷን በማካፈል አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገች ትገኛለች፡፡

በ2016 ዓ.ም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በአዘርባጃን ይፋ የሥራ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ሀገራቱ በፐብሊክ ሰርቪስ ዘርፉ ቀልጣፋና ተጠያቂነት የሰፈነበት አሰራርን ዕውን ለማድረግ በትብር ለመስራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

በተጨማሪም በመረጃ፣ በጸጥታና ደኅንነት ዘርፎች የጋራ ትብብር አቅም ግንባታና ሀገራቱን ተጠቃሚ በሚያደርጉ ሌሎች ፕሮጀክቶችን በጋራ ለመፈጸም ተስማምተው በቅንጅት እየሰሩ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅትም ሁለቱ ሀገራት በተለያዩ ዘርፎች ያላቸው ሁለንተናዊ ትብብር እየተጠናከረ በመምጣት አዲስ ምዕራፍ ላይ ይገኛል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ልዑካቸው ከትናንት ጀምሮ በአዘርባጃን እያደረጉት የሚገኘው ይፋዊ የሥራ ጉብኝትም እያደገ የመጣውን የሀገራቱን ሁለንተናዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ያስችላል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ጉብኝት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በጠንካራ ትብብር እየጎለበተ የመጣውን የሁለቱን ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይበልጥ የሚያጸና እንደሆነም ታምኖበታል፡፡

በመላኩ ገድፍ