አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከአዘርባጃን ጋር ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተደረጉ ትብብሮች አጋርነታችን እያደገ መጥቷል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መረጃ፤ በአዘርባጃን ባደረግኩት የመጀመሪያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ፕሬዚዳንት ኢልሃም አሊዬቭ ላደረጉልኝ ሞቅ ያለ እና የተከበረ አቀባበል ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ ብለዋል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአቪዬሽን ዘርፍ፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች እና በነፃ የንግድ ቀጣናዎች እንዲሁም በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና በአዘርባጃን አቻው መካከል በተደረጉ የኢኮኖሚ ትብብሮች ላይ በመመስረት አጋርነታችን በየጊዜው እያደገ መጥቷል ሲሉ ገልጸዋል።
እነዚህ የትብብር ዘርፎች ለሁለትዮሽ ግንኙነታችን መጠናከር መሠረት የጣሉ ናቸው ብለዋል።
ዛሬ ባደረግነው ጥልቅ ውይይትም ግንኙነታችንን እና ትብብራችንን ይበልጥ ለማጠናከር እና ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ተስማምተናል ነው ያሉት።
በዛሬው ዕለትም በመከላከያ እና በሌሎች ዘርፎች ዙሪያ የመግባቢያ ሰነዶች ፊርማ ሥነ-ሥርዓት ላይ መገኘታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።