የሀገር ውስጥ ዜና

አብሮ አደግ እህትማማቾችን በሀሳብ ያፋጠጠው ፋና መድረክ…

By Melaku Gedif

February 27, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሒክማ ከይረዲን እና ነቢሃ መሀመድ ይባላሉ፤ የፖለቲካ እሳቤ ልዩነት ያላቸው አብሮ አደግ እህትማማች ፖለቲከኞች ናቸው።

ወ/ሮ ሂክማ ብልፅግናን፤ ወይዘሮ ነቢሃ ደግሞ ነፃነትና እኩልነት ፓርቲን ወክለው ዛሬ በጤና ርዕሰ ጉዳይ በተካሄደው ፋና መድረክ ክርክር አድርገዋል፡፡

አብሮ አደግ እህትማማቾቹ ዘር መጋራታቸው የፖለቲካ የሃሳብ ልዩነት እንዳይኖራቸው አላደረጋቸውም።

ፖለቲከኞቹ ለኢትዮጵያ ይበጃል በሚሉት የፖለቲካ እሳቤ ይለያያሉ፤ ይህ ልዩነታቸውም ይመስለናል ወደሚሏቸው ሁለት የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲቀላቀሉ አድርጓቸዋል፡፡

“የፖለቲካ ልዩነት ያለና የነበረ ነው” የሚሉት ፖለቲከኞቹ ÷ ልዩነታቸው እህትማማችነታቸው ላይ ተፅዕኖ እንደሌለው ያስረዳሉ፡፡

ሁለቱም አብሮ አደግ እህትማማች ለቀጣዩ ጠቅላላ ምርጫ የፓርቲያቸውን እሳቤ በማስተዋወቅ ረገድ በትኩረት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

ዛሬ በተካሄደው የፋና መድረክ ክርክርም ሂክማ ብልፅግናን ወክለው “መከላከልና አክሞ ማዳን ያማከለ” የጤና ፖሊሲን፤ ነቢሃ ደግሞ “በለዘብተኛ ሊበራሊዝም” የተቃኘውን የጤና ፖሊሲ ይዘው ተሟግተዋል፡፡

አብሮ አደግ እህትማማች ፖለቲከኞቹ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት÷ “ልዩነት እርግማን አይደለም፤ የሀሳብ ልዩነትን በሰለጠነ መንገድ መፍታት ግን መሰልጠን ነው፡፡”

በአፈወርቅ እያዩ