የሀገር ውስጥ ዜና

የትግራይ ክልል አሁን ከገባበት ችግር ለመውጣት ሀገራዊ ምክክር ቁልፍ መሳሪያ ነው

By Melaku Gedif

February 27, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የትግራይ ክልል አሁን ከገባበት ችግር ለመውጣት ሀገራዊ ምክክር ቁልፍ መሳሪያ ነው አሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከትግራይ ክልል ከመጡ እና በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

በመድረኩ በክልሉ የሚደረገውን የምክክር ሒደት ለማስጀመር የተለያዩ አማራጭ ምክረ ኃሳቦችን መሰብሰብ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ተደርጓል፡፡

መሥፍን አርአያ (ፕ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የትግራይ ክልል አሁን ከገባበት ችግር ለመውጣት ሀገራዊ ምክክር ቁልፍ መሳሪያ ነው።

ሒደቱ የቁጥር ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የተሳትፎ ጉዳይ እንደመሆኑ ያለ ትግራይ ክልል ተሳትፎ ምክክሩ ምሉዕ እንደማይሆን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ ስለሚያከናውናቸው ዐበይት የሥራ ክንውኖችና ቀጣይ ተግባራት ማብራሪያ የሰጡት ዋና ኮሚሽነሩ÷ በዚህም በትግራይ ክልል የምክክር ሒደት ለመጀመር የተደረጉ ጥረቶችን አንስተዋል።

በሒደቱ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በማንሳት የመድረኩ ተሳታፊዎች ለችግሮቹ መፍትሔ እንዲፈልጉና ለሒደቱ ስኬት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።