በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የነበሩት ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም በዓድዋው የጦር ግንባር በመሰለፍ ያዩትን በሕይወት ታሪካቸው ጽፈውታል፡፡
ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ባሉት ሳምንታት የአካባቢው እረኞች ሲጫወቱ ደበሎ እየሰቀሉ አዋጅ ይናገሩ እንደነበር አዋጁንም በመጥቀስ ጽፈውታል:-
«እሽ ስማ ብለውሃል መስማሚያ አይንሳህ «ያድባርን ያውጋርን ጠላት… «ሐማሴንን ለራስ አሉላ፣ አዲግራትና አካባቢውን ተምቤንን ለራስ ስብሐት፣ እንደርታን ዋጀራትን ለደጃዝማች ሐጎስ፣ እንዳመኾኒ ሰለሞንን ለፊታውራሪ ተክሌ፣ «ዋድላን ደላንታን ለፊታውራሪ ገበየሁ፣ ሰጥቻለሁ ብለውሃል! ይበጅ ያድርግ፤ «በየካቲት ጣጣችን ክትት «በመጋቢት እቤታችን ግብት «በሚያዛሳ ያገግም የከሳ «ይበጅ ያድርግ…» እያሉ ይተነባሉ(ይለፍፋሉ/ይናገራሉ)፡፡
ስለ ጦርነቱ ውሎም እንዲህ ተርከውታል:-
የሰው ብዛት እንደ ጎርፍ ሆነ፡፡ እግረኞችም በቅሎኞችም ተደባልቀን እንርመሰመሳለን፡፡ ፈረሰኞች በጎን እያለፉን ይቀድማሉ፡፡ ይሮጣሉ! እንደተቻለን እንሽቀዳደማለን፡፡
ጠመንጃ ሲንጣጣ ሰማን፣ መድፍ ወዲያው ያጓራ ጀመር፡፡
ተኩሱ እያደር እየባሰበት ተቃረበን፣ አረሮቹ ማፏጨት ጀመሩ፡፡
የቆሰሉ ሰዎች ተቀምጠው አገኘን፡፡ አያ ታደግ እጁን ተመትቶ ከመንገዱ ዳር ከዛፍ ሥር ተቀምጧል፡፡ ገና በሩቁ አይቶን ተጣራ፣ ቁስሉን በመቀነቱ አሰርንለት፡፡ ጥለነው እንዳንሄድ ለመነን፣ ፈይሣ ጠመንጃ የለውም፤ የቁስለኛውን ጠመንጃ ተሸከመና እዚያው ቀረ፡፡
እኔ ወደ ግምባር አለፍኩ፡፡ የማውቀውን ሰው አንድም አላጋጠመኝም፡፡ ተኩስ ስለበዛ መሮጥ የማይቻል ሆነ፡፡ የሰውም ብዛት እንደልብ አያስኬድም፡፡
ደጃዝማች ማናዬ እና ልጅ አስፋው (ልጃቸው) ሁለቱም ቆስለው ድንጋይ ተንተርሰው ተጋድመው አገኘኋቸው፡፡
ልጅ አስፋው (በኋላ ፊታውራሪ አስፋው) አወቀኝና ጠቀሰኝ፡፡ እኔም አልፌ ወደ ግምባር ሮጥኩ፡፡ ጦራችን ተደባልቋል፡፡ ሰውና ሰው አይተዋወቅም፡፡
ሴቶች ገምቦ ውሃ እያዘሉ፣ በበቅሎቻቸው እንደተቀመጡ፣ ለቁስለኞች ውሃ ያቀርባሉ፡፡ ሲነጋገሩ ሰማኋቸው፡፡ «ኧረ በጣይቱ ሞት» ይላሉ፡፡ እቴጌ የላኳቸው ይሆናሉ እያልኩ አሰብኩ፡፡
ነጋሪቱ ከግምባርም፣ ከጀርባም፣ ከቀኝም ከግራም ይጎሸማል፡፡
የተማረኩ ጣልያኖችን አየሁ፡፡ ወዲያው ምርኮኞቹ በዙ፣ አንዳንዶቹ ወታደሮች፣ ይበልጡን/ብዙ ጣልያኖችን እየነዱ መጡ፡፡
በኋላ የምርኮኞች ብዛት ለዐይን የሚያሰለች ሆነ፤ ድል ማድረጋችንን አወቅሁ፡፡
ጣልያኖች መዋጋታቸውን ትተው ማርኩን እያሉ ይለምናሉ፡፡ እንደዚህ የዓድዋ ጦርነት ዕለት አንድ ጥይት እንኳ ሳልተኩስ ጦርነቱ አለቀ፡፡
የተክለ ሐዋርያት ምልከታ የበርክሌን አገላለጽ እንዲህ ያስታውሰዋል::
በጳውሎስ ኞኞ “አጤ ምኒልክ” ላይ እንደተጻፈውም “የተተከለው ድንኳን ሲታይ ከብዛቱ የተነሳ አፍሪካ አውሮፓውያን ቅኝ ገዥዎችን ለመጠራረግ የተነሳች ይመስላል፡፡ የጦርነቱ ዕለት ኢትዮጵያውያኑ ደማቅ ቀለም ያለው ካባ ለብሰው፣ ጠመንጃና ጦር ይዘው፣ ጎራዴ ታጥቀው፣ የነብርና የአንበሳ ቆዳ ለብሰው፣ አዝማሪዎቹ እየዘፈኑ ቄሶች፣ ልጆች፣ ሴቶች ሳይቀሩ ፀሐይዋ ፈንጠቅ ስትል በተራራው ላይ በታዩ ጊዜ የጣሊያንን ጦር አሸበሩት፡፡”