የሀገር ውስጥ ዜና

ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚቀላቀሉ ተማሪዎች ቁጥርን ለማሳደግ…

By Yonas Getnet

February 28, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚቀላቀሉ ተማሪዎች ቁጥርን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው አለ የክልሉ ትምህርት ቢሮ።

ቢሮው ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ያለመ መርሐ ግብር ማስጀመሪያ መድረክ በወራቤ ከተማ እያካሄደ ይገኛል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ በክልሉ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የሚቀላቀሉ ተማሪዎች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ በትኩረት ሊሰራ ይገባል።

ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በተደረገ ጥረት የተማሪዎች ውጤት መሻሻል መኖሩን ገልጸው÷ በ2015 ዓ.ም ወደ ዩኒቨርሲቲ የመግባት ምጣኔው 2 ነጥብ 7 ከነበረበት በ2017 ወደ 5 ነጥብ 96 በመቶ ማሳደግ መቻሉን አንስተዋል።

በ2017 ዓ.ም 107 ትምህርት ቤቶች ተማሪ ማሳለፍ አለመቻላቸውን አንስተው÷ ባለፉት ዓመታት የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ተማሪዎችን በማስፈተን ውጤት ያላስመዘገቡ ትምህረት ቤቶችን በመለየት ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

ክልሉ ችግሩን ለመፍታት ከሚያደርገው ጥረት ባለፈ ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ኢዱኬሽን ዴቭሎፕመንት ትረስት ጋር በመቀናጀት 63 ትምህርት ቤቶችን ለመደገፍ ከስምምነት ላይ መድረሱን አመልክተዋል።

ትምህርት ቤቶች ብቁ ዜጋ ማፍራት እንዲችሉ በሚቀጥሉት 5 ዓመታት በመምህራንና በአመራር አቅም ማጎልበት እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ተቋሙ እንደሚሰራም ተገልጿል።

በብርሃኑ በጋሻው