አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዓድዋ የአፍሪካ ሀገራት ሲያደርጉት የነበረውን የፀረ ቅኝ ግዛት ትግል ያጠናከረ የድል በዓል ነው አሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፡፡
በአዲስ አበባ የሚገኘው ‘ግሎባል ብላክ ሴንተር’ ዓመታዊ የምክር ቤት ስብሰባውን በዓድዋ ድል መታሰቢያ እያካሄደ ነው።
ፕሬዚዳንት ታዬ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት÷ የዓድዋ ድል ሌሎች አፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ለመውጣት ሲያደርጉ የነበሩትን ትግል ያነሳሳ እንደነበር አውስተዋል፡፡
የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ የራሷን ታሪክ በራሷ እንድትፅፍ እና እንድትተርክ ያደረገ እንዲሁም የኢትዮጵያ ባህልና ቅርስ ለቀጣዩ ትውልድ መተላለፍ እንዲችል ያደረግ በዓል መሆኑም አብራርተዋል፡፡
‘ግሎባል ብላክ ሴንተር’ ዓመታዊ የምክር ቤት ስብሰባ ላይ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮችን ጨምሮ የማዕከሉ አባላት እና ዓለም አቀፍ ደጋፊዎች ተገኝተዋል።