አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዘንድሮ 130ኛ ዓመት በዓሉ ላይ የሚገኘው የዓድዋ ድል ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ እንዲሁም ለመላ ጥቁር ህዝቦች የነጻነት ቀንዲል አብርቷል።
የዓድዋ ድል መገኘት ፓን አፍሪካኒዝም መሰረት እንዲይዝ በእጅጉ አግዟል፤ አፍሪካ ዕጣ ፈንታዋ ቅኝ ግዛት ነው የሚለውን አስተሳሰብ በመገርሰስ የነጻነት ችቦ ለኩሶ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ራሳቸውን ነጻ ለማውጣት ትግል እንዲጀምሩ አድርጓል።
በዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ጀግኖች ስም እና ዝና በዓለም እንዲናኝ እንዲሁም ለጥቁር ህዝቦች አረዓያ እንዲሆኑ መንገድ ከፍቷል።
ድሉ በኋላ ላይ የአፍሪካ ህብረት የሚለውን ስያሜ የያዘው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በአዲስ አበባ እንዲመሰረት ኢትዮጵያም የተቋሙ ማዕከል ሆና እንድትቀጥል የላቀ ሚና ነበረው።
አሜሪካን ጨምሮ በተለያየ ክፍለ ዓለም በሚገኙ ጥቁር ህዝቦች ዘንድ የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ እንዲጠናከር አስችሏል።
በዳግም የፋሺስት ጣሊያን ወረራ ወቅት በርካታ አፍሪካ አሜሪካኖች ከኢትዮጵያ ጎን በመሰለፍ ከገንዘብ ድጋፍ ባለፈ ዘመቻውን በመቀላቀል አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ የዓድዋ ድል የራሱ አስተዋጽኦ ነበረው።
የአፍሪካ የነጻነት ታጋዮች ኢትዮጵያ ላይ የተፈጸመውን ዳግም ወረዳ በመቃወም እና በየሀገራቱ ድምጻቸውን በማሰማት በወራሪው የጣሊያን ጦር ላይ ጫና ፈጥረዋል።
በመሆኑም የዓድዋ ድል የቅኝ ግዛት ሰንሰለትን በጥሷል፤ ኢትዮጵያንም የነጻነት ተምሳሌት እንድትሆን አስችሏል።