ከ130 ዓመታት በፊት የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ኢትዮጵያ የነጩን ዓለም ያናወጠ፣ ለጥቁር ሕዝቦች ሞገስን እና የይቻላል መንፈስን ያላበሰ ብስራት ተሰማ፡፡
በዚህ የታሪካዊ ገድል የተደመመው ጆርጅ በርክሌ በመጣጥፉ ያንፀባረቀውን አጤ ምኒልክ በተሰኘው የጳውሎስ ኞኞ መጽሐፍ ላይ እንደሚከተለው ሠፍሯል፡፡
«ሃያ ሺሕ ያህል ወታደሮች ያሉበት የአውሮፓ ጦር በአፍሪካ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ተሸነፈ፡፡ በእኔ እምነት መሠረት በዘመናችን ታሪክ ውስጥ እንደ ዓድዋው ያለ ጦርነት የለም፡፡ 25,000 ሰዎች በአንድ ቀን ጀንበር የሞቱበትና የቆሰሉበት ነው፡፡ ፖለቲካና ታሪክ አበቃ፡፡ ጥቁሮች ብርቱ ሕዝቦች መሆናቸው ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ ተጽፎላቸዋል፡፡ »
ከዓድዋ ጦርነት አሥር ዓመታት በፊት 14 የአውሮፓ አገሮች በርሊን ላይ ባደረጉት ስብሰባ አፍሪካን ለመቀራመት ሲወስኑ የጣሊያን ድርሻ ኢትዮጵያ ነበረች፡፡
ኢትዮጵያ ቅድመ ዓድዋ ከወራሪዎችና ከኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ጋር ተዋግታ ድል መታለች፡፡
አንዱ በአፄ ዮሐንስ አራተኛ ዘመን በጥር 1879 ዓ.ም ዶግዓሊ ላይ በራስ አሉላ አዝማችነት በጣሊያን ላይ ለመጀመርያ ጊዜ የተቀዳጀችው ድል ነበር፡፡
ጣሊያን ያዘመተችው 500 ወታደሮች ለወሬ ነጋሪ ሳይተርፉ የተደመሰሱበት ነበር፡፡
በ19ኛው ምዕት ዓመት ሁለተኛው አጋማሽ ጀምሮ በመቅደላ (እ.ኤ.አ. 1868) ከእንግሊዝ፣ በጉንደትና በአውሳ፣ በጉራዕ (1875 እና 1876) ከግብፅ፣ በመተማ (1889) ከደርቡሽ፣ በኮአቲትና ሰንአፈ (1895) ከጣሊያን ጋር ጦርነት ገጥማ በድል ተወጥታለች፡፡
የዘመኗ ጣሊያን የቅኝ ግዛት ሕልሟን እውን ለማድረግ ስትነሳ በ1888 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ለማድረግ ምክንያት የሆነው የውጫሌው ውል ነበር፡፡
ይህም በአንቀጽ 17 በጣሊያንኛ ትርጉሙ ኢትዮጵያ የጣሊያን ጥብቅ ግዛት ነች፡፡ የውጭ ግንኙነቷ በርሷ በኩል ይሆናል የሚለው ሐረግ ነው፡፡
ጦርነቱ አይቀሬ መሆኑ ሲታወቅ ንጉሠ ነገሥቱ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሕዝቡንና የየአካባቢውን መኳንንትና ገዢዎች በጣሊያን ቅኝ ገዢ ላይ እንዲነሱ የአገርን ክብርና ነፃነት እንዲያስጠብቁ አዋጅ አስነገሩ፡፡
“… አሁንም አገር የሚያጠፋ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባሕር አልፎ መጥቷል . . . በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ . . . ያገሬ ሰው . . . ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ፡፡ ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በኀዘን እርዳኝ፡፡”
ኢትዮጵያውያንም የርስ በርስ ግጭታቸውን፣ ውስጣዊ ችግሮቻቸውንና አለመግባባታቸውን ወደ ጎን ትተው ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ተጠራርተው እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ፣ እንደ አንድ ልብ መስካሪ ሆነው ወደ ጦር አውድማው ተመሙ፡፡ በንጉሠ ነገሥቱ ጠቅላይ አዝማችነት 120,000 ተዋጊ ተሰለፈ፡፡
የዓድዋ አዝማቾች ዳግማዊ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ፣ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት፣ ራስ መንገሻ ዮሐንስ፣ ራስ አሉላ፣ ራስ መኰንን፣ ራስ ሚካኤል፣ ራስ ወሌ፣ ራስ ስብሐትና ደጃዝማች ሐጎስ ተፈሪ፣ ራስ አባተ፣ ፊታውራሪ ገበየሁ፣ ደጃዝማች ባልቻ፣ ዋግ ሹም ጓንጉል እና ሌሎችም ነበሩ፡፡
የጣሊያን ወታደሮች የሚመሩት በጄኔራል ባራቴሪ ሲሆን አራት ጄኔራሎችም ክፍለ ጄኔራል አልቤርቶኒ፣ ጄኔራል ኤሌና፣ ጄኔራል አሪሞንዲና ጄኔራል ዳቦርሚዳ ጦሮቻቸውን ይመራሉ፡፡
ተክለ ጻድቅ መኩሪያ አፄ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት በሚባለው መጽሐፋቸው እንዳስቀመጡት፣ የጣሊያንንም ወታደር ከበው እየተፏከሩ በጥይትና በጎራዴ ሲደበድቡት የኢጣሊያ ጦር አራት ሰዓት ከተዋጋ በኋላ ሽሽት ጀመረ፡፡
በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያውያን እየተከታተሉ ሲወጉት፣ አዝማቹ ጄኔራል አልቤርቶኒ ተቀምጦበት የነበረው በቅሎ ተመቶ ወደቀ፡፡
ወዲያው ተነሥቼ አመልጣለሁ ብሎ ለመነሣት ሲጥር ከቅምጡ ሳይነሳ እየተሽቀዳደሙ የሚሮጡት ኢትዮጵያውያን ደርሰው ጄኔራሉን ማረኩት፡፡
የ1ኛው ክፍለ ጦር አዛዡ ተማርኮ፣ ሠራዊቱ በጭራሽ ከጠፋ በኋላ ሁለተኛው ክፍል የጦር ሠራዊት ራአዮ ከሚባለው ስፍራ ላይ ሆኖ፣ ከአራት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ የሦስተኛውን ክፍል የጄኔራል ኤሌናን ጦር ጨምሮ ተዋግቶ በመጨረሻ የጦር አዛዡ ጄኔራል አሪሞንዲ እዚያው ጦርነቱ ላይ ሞቶ ተገኘ፡፡
ከዚህም በኋላ በመጨረሻ ያለው የጣሊያን ጦር በተለይ ማርያም ሸዊቶ ከሚባለው ስፍራ ላይ ተጋጥሞ ከቀድሞው የበለጠ ጦርነት ተደረገ፡፡
ይልቁንም የመጨረሻው ድል የሚፈጸምበት በመሆኑ የሁለቱም የጦር ሠራዊት ተደባልቆ በጨበጣ በሚዋጉበት ጊዜ፣ በጨበጣ በሚደረገው ዘመቻ ከኢጣሊያኖች ይልቅ ኢትዮጵያውያን በጎራዴ አነዛዘር የቀለጠፉ ነበሩ፡፡
ይሁን እንጂ ጣሊያኖች ተስፋ በቆረጠ ኃይል እስከ አሥራ ሁለት ሰዓት ድረስ ሲዋጉ በመጨረሻ አዛዣቸው ጄኔራል ዳቦርሚዳ በጥይት ደረቱን ተመቶ ወድቆ በጠብታ ውሃ አፌን አብሱልኝ ሲል ሲጮኽ ቆይቶ ሞተ፡፡
በዓድዋ ጦርነት በስለላው የጣሊያንን የጦር እቅድ በማሳከር አኩሪ ተግባር የፈጸመው ባሻዬ አውአሎም ሐረጎት ነው፡፡ ባሻዬ አውዓሎም የባዕዳኑ አገልጋይ የነበረ ሲሆን በቁጭት በመነሳሳትና በብላታ ገብረእግዚአብሔር ጊላ አማካይነት ከራስ መንገሻ ዮሐንስ ጋር ይገናኛል፡፡
ቀኛዝማች ታደሰ ዘወልዴ ታሪኩን በመጽሐፋቸው እንደገለጹት፣ ራስ መንገሻም ከአፄ ምኒልክና ከእቴጌ ጣይቱ ጋር ይገናኙና የጦርነቱ ጊዜ ሲቃረብ የተሳከረውን እቅድ ለጄኔራል ባራቲየሪ እንዲደርስ ይደረጋል፡፡
የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም አውዓሎምና ብላታ ገብረ እግዚአብሔር ከጣሊያናውያን ተለይተው ወደ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸው ገብተው ጦርነቱ ሲፋፋም ከጣሊያን መኰንኖች አንዱ «አውዓሎም አውዓሎም» እያለ ሲጣራ አውዓሎም ሰምቶ፣ «ዝወኣልካዮ ኣያውዕለኒ» (ከዋልክበት አያውለኝ) ብሎ አፌዘበት ይባላል፡፡