አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) ከአዘርባጃን ጋር በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ አብረን ለመስራት ተስማምተናል አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው እና ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ጋር ከየካቲት 19 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዘርባጃን የነበራቸውን ይፋዊ የስራ ጉብኝት አጠናቅቀዋል።
የልዑካን ቡድኑን ቆይታ አስመልክተው ማብራሪያ የሰጡት ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር)፤ የልዑካን ቡድኑ የአዘርባጃንን የቴክኖሎጂ ተቋማት በተለይም የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ አካዳሚን እና የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ጎብኝቷል።
በዚህም ለኢትዮጵያ የሚጠቅሙ ተሞክሮዎች መወሰዳቸውን አመልክተዋል።
ከተቋቋመ 1 ዓመት ተኩል የሆነው የሀገሪቱ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ አካዳሚ ሁሉንም ዘርፍ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እያስተሳሰረ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
በትምህርት ዘርፍ ቀደም ሲል የነበረው የመማር ማስተማር ሂደት ሙሉ ለሙሉ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መተካቱን በአብነት አንስተዋል።
ህዝቡ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እንዲጠቀም የተደረገው ጥረት የሚበረታታ ነው ብለዋል።
የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ተቋም ካቋቋመች ስድስት ዓመት ከሆናት ኢትዮጵያ ጋር ተሞክሮ ለመቀያየር እና በትብብር ለመስራት አዘርባጃን ፍላጎት እንዳላትም ጠቁመዋል።
የአዘርባጃን የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከኢትዮጵያ መሶብ የአንድ ማዕከል ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው ጠቅሰው፤ በማዕከላቱ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስን የመጠቀም ልምድ የዳበረ መሆኑን ተናግረዋል።
በአንድ ማዕከል አገልግሎት አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን መጠቀም ወሳኝ መሆኑ ትምህርት የተወሰደበት እንደሆነ ገልጸዋል።
በአጠቃላይ በዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና በትውልድ ላይ አዘርባጃት የምትሰራው ስራ አመርቂ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሁለቱ ሀገራት በትብብር ለመስራት መስማማታቸውን ጠቅሰዋል።
ይህም የሀገራቱን ተሞክሮ በመጋራት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን እውን ለማድረግ እገዛ ይኖረዋል ብለዋል።
በአቢይ ጌታሁን