የሀገር ውስጥ ዜና

 በአዘርባጃን የተደረገው ጉብኝት የሀገራቱን ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር ነው – ቢልለኔ ስዩም

By Mikias Ayele

February 28, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ልዑካቸው በአዘርባጃን ያደረገው ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር ነው አሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው እና ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ጋር በአዘርባጃን የነበራቸውን ይፋዊ የስራ ጉብኝት አጠናቅቀው ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል።

ይፋዊ የስራ ጉብኝቱን አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊዋ÷ ላለፉት ጥቂት ዓመታት ኢትዮጵያ እና አዘርባጃን ግንኙነታቸው እየተጠናከረ መምጣቱን አንስተዋል፡፡

ሀገራቱ የነበራቸው ትስስር ባለፉት ሁለት አመታት የበለጠ መጠናከሩን ጠቅሰው÷ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን እና የአዘርባጃን ኤምባሲ በአዲስ አበባ መከፈቱን ተናግረዋል፡፡

ቀደም ሲል በሀገራቱ  መካከል የተለያዩ ኢኮኖሚ ትብብሮች ሲደረጉ እንደነበር አስታውሰው፤ በአቪዬሽን እና ኢንቨስትመንት ዘርፎች የልምድ ልውውጦች ሲደረጉ መቆየታቸውን አብራርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ልዑካቸው ያደረጉት ጉብኝት እና በመሪዎች ደረጃ  የተደረጉ ውይይቶች የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የበለጠ የሚያጠናክር መሆኑንም አስረድተዋል።

በውይይቱ በኢነርጂ፣ በኢንቨስትመንት፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በመከላከያ ዘርፎች እና በአየር ንብረት ለውጥ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት መደረሱን ገልጸዋል፡፡

በተለይም አዘርባጃን የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ጉባዔን (ኮፕ29) ማስተናገዷን አስታውሰው፤ በውይይቱ ኢትዮጵያ የምታስተናግደውን ኮፕ32 በስኬት ለማጠናቀቅ የሚያስችል ልምድ ከአዘርባጃን መውሰዷን ጠቅሰዋል፡፡

ከውይይቱ በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ልዑካቸው በባኩ ከተማ የመሰረተ ልማት ግንባታ ልምድ መቅሰም የሚያስችል ጉብኝት ማድረጉን ገልፀዋል፡፡

በሚኪያስ አየለ