የሀገር ውስጥ ዜና

የተፈረሙት ስምምነቶች የትብብር ዘርፎችን ለማስፋት የሚያስችሉ ናቸው – ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)

By Mikias Ayele

February 28, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከአዘርባጃን ጋር የተፈረሙት ስምምነቶች ወደ ፊት የትብብር ዘርፎችን ለማስፋት እገዛ የሚያደርጉ ናቸው አሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ልዑካን ቡድናቸው በአዘርባጃን የነበረውን ይፋዊ የስራ ጉብኝት አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)÷ ላለፉት ጥቂት ዓመታት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የትብብር አድማስ እየሰፋ መጥቷል ብለዋል።

በመሪ ደረጃ ጉብኝት መካሄዱ በተለያዩ መስኮች ያለውን ትብብር ይበልጥ ያጠናክራል ነው ያሉት።

በአዘርባጃን የተደረገው ደማቅ አቀባበል የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ለማጠናከር ፍላጎት እንዳለ ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈረሙት ስምምነቶች ወደ ፊት የትብብር ዘርፎችን ለማስፋት እገዛ የሚያደርጉ እንደሆኑም ጠቅሰዋል።

በዲጂታል የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ የአዘርባጃን ተሞክሮ ከኢትዮጵያ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ ረገድ አገልግሎቱን ለማሻሻል በትብብር መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

በቱሪዝም፣ በአየር ንብረት ለውጥ ዲፕሎማሲ እና በአቪዬሽን ዘርፎች የሀገራቱን ግንኙነት ተቋማዊ በማድረግ ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ስምምነቶቹ ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል ብለዋል።

በሀገራቱ መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ግንኙነት በተለይም የንግድ እና ኢንቨስትመንት ትስስርን ለማሳደግ የጎላ ፋይዳ እንደሚኖራቸው አመልክተዋል።

በአቢይ ጌታሁን