አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓድዋ ድል ለአፍሪካዊያን የጋራ ደኅንነትና ወታደራዊ ትብብር ትልቅ መሠረት ነው አሉ የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢ/ር)፡፡
2ኛው የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ጉባኤ “ከአኩሪ ታሪክ፣ ወደ ብሩህ አድማስ” በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የዓድዋ ድል የአፍሪካውያን የነፃነት ፋና ወጊ ከመሆኑ ባለፈ ለዛሬው አህጉራዊ ትብብር ዋነኛ መነሻ ነው፡፡
አፍሪካውያን በዓድዋ ድል የታየውን የይቻላል መንፈስ በመሰነቅ በትብብርና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተ አህጉራዊ የጸጥታና ወታደራዊ ትብብርን ይበልጥ ማጠናከር ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።
የአፍሪካ ሀገራት አሁን ያለውን ተለዋዋጭና ውስብስብ የዓለም የፖለቲካና የጸጥታ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት የሁለትዮሽና አህጉራዊ ትብብራቸውን በማጠናከር ከመቼውም ጊዜ በላይ በጋራ ሊቆሙ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ድሉ ኢትዮጵያውያን ያለ ምንም ልዩነት በጋራ በመቆም ያሳኩት የቆራጥነትና የአልገዛም ባይነት ውጤት መሆኑን አውስተው፥ ይህ አንድነት ዛሬም ለአፍሪካ ሰላምና ደኅንነት ዋስትና መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የዓድዋ ድል በአፍሪካና በሌሎች ዓለማት የሚገኙ ሕዝቦች ለፍትሕ፣ ለእኩልነትና ለነፃነት እንዲታገሉ መንገድ የከፈተ ታሪካዊ ገድል ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በጉባኤው ላይ የአፍሪካ ሀገራት መከላከያ ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች፣ ወታደራዊ አታሼዎችና ተመራማሪዎች እንዲሁም የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት ኃላፊዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።