አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓድዋ ድል በደምና አጥንት ዋጋ ተከፍሎ ጭቆና ውስጥ ለነበሩ ሁሉ የድል ጮራ የሆነ አኩሪ ታሪካችን ነው አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡
የዘንድሮው የዓድዋ ድል በዓል በአዲስ አበባ ከተማ “ከአኩሪ ታሪክ ወደ ብሩህ አድማስ“ በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ ይገኛል፡፡
ከንቲባ አዳነች 130ኛውን የዓድዋ ድል በዓል የዓድዋ ዘማቾች መነሻ በሆነውና የጀግኖች የተጋድሎ ታሪክ በሚመጥን መልኩ እዲዘከር በተገነባው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ከአዲስ አበባ ወጣቶች ጋር በፓናል ውይይት አክብረዋል፡፡
ከንቲባዋ በዚህ ወቅት ÷ በደምና በአጥንት ዋጋ ተከፍሎ ለጥቁር ህዝቦች እና በጭቆና ውስጥ ለነበሩ የሰው ልጆች ሁሉ የድል ጮራ የሆነውን አኩሪ ታሪካችንን ከወጣቶቻችን ጋር በታላቅ ድምቀት ዘክረነዋል ብለዋል።
ከዓድዋ ድል የምንማረው የአንድነት እና የፅናትን አይበገሬነትና አሸናፊነት ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች÷ በወቅቱ የአመለካከትና የአስተሳሰብ ልዩነቶች እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡
ይሁን እንጂ አገር ተነካ ሲባል እንደ አንድ ልብ መካሪና እንደ አንድ አፍ ተናጋሪ ሆነው በአንድነና በጀግንነት ወራሪውን ኃይል ድል እንደነሱት አውስተዋል፡፡
በእኛም ዘመን የራሳችንን ትውልድ ተሻጋሪ ታሪክ ለመስራት የዓድዋን መንፈስ ታጥቀን በፅናትና ሁላችንም በአንድነት ተግዳሮቶችን ተቋቁመን፣ የታላቁን የሕዳሴ ግድብ ግንባታ በማከናወን የ“አይቻልም” መንፈስን ሰብረን የዳግማዊ ዓድዋን ታሪክ ሰርተናል ብለዋል።
እንዲሁም በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በስንዴ ልማትና በከተሞቻችን ትራንስፎርሜሽን የልማት አብዮቶች የዳግማዊ ዓድዋ ድሎችን ፈፅመናል ነው ያሉት።
የዛሬው ውይይት ወጣቱ ትውልድ የቀደምት አርበኞችን አደራ፣ ታሪክና ጀግንነት በመውረስ የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት፣ ጽናትና አንድነት በከፍተኛ የሀገር ፍቅር ስሜት የገለጸበት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ይህ ትውልድ ለተግዳሮቶች ሳይበገር “አይቻልም” የሚለውን አስተሳሰብ በመቻል የቀለበሰ፣ የራሱን አንፀባራቂ ታሪክ የሰራ፣ የታሪኩ አውራሽና ለአዳዲስ ድሎች የተዘጋጀ አሸናፊ ትውልድ ነው ሲሉም አውስተዋል።
ወጣቱ በቀጣይ የዓድዋ ድል አደራ የሆነውን አንድነት በማጠናከር፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ፣ ሰላምን በማስጠበቅና የባህር በር ፍትሐዊ ጥያቄ ምላሽ እንዲገኝ በማድረግ ረገድ ሚናውን ይበልጥ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ማረጋገጡንም አመልክተዋል፡፡