የሀገር ውስጥ ዜና

ዓድዋ በጀግንነትና በአይበገሬነቱ ህያው ሆኖ የሚኖር የድል ስንቅ ነው – አይሻ መሀመድ (ኢ/ር)

By Adimasu Aragawu

March 02, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዓድዋ በጀግንነትና በአይበገሬነቱ ህያው ሆኖ የሚኖር የድል ስንቅ ነው አሉ የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሀመድ (ኢ/ር)።

130ኛው የዓድዋ ድል በዓል “ከአኩሪ ታሪክ ወደ ብሩህ አድማስ” በሚል መሪ ሐሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል።

ሚኒስትሯ በበዓሉ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት÷ የመከላከያ ሠራዊቱ የሀገራችንን ሉዓላዊነትና የሕዝባችንን ሰላም በፅኑ መሰረት ላይ ከማቆም ባለፈ የነፃነት ዘብ በመሆን የማይተካ መስዋዕትነት እየከፈለ ይገኛል ብለዋል።

ዓድዋ በጀግንነት፣ በወኔ፣ በዲሲፕሊንና በአይበገሬነቱ ህያው ሆኖ የሚኖር የድል ስንቅ መሆኑን ተናግረዋል።

በዓሉን ስናከብር በአባቶቻችን የነፃነት ገድል ላይ በመቆም ወደ ላቀ ሁለንተናዊ ሉዓላዊነትና ብሩህ ሀገራዊ ከፍታ የምናሸጋግርበት የታሪክ አደራችንን በሥራና በትጋት የምንወጣበት አዲስ የድል ምዕራፍ መሆኑን በማረጋገጥ ሊሆን ይገባልም ነው ያሉት።

የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን መላው የሰው ልጆች ለክብራቸውና ለነፃነታቸው ያደረጉት ተጋድሎ በድል የተመሰከረበት፣ የጥቁር ሕዝቦች የትንሳኤ ብስራትና የሰው ልጅ ለማንነቱና ለሉዓላዊነቱ የከፈለው ወደር የለሽ መስዋዕትነት የድል አክሊል የደፋበት የታሪክ ማማ መሆኑንም ገልጸዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ፣ አፈ ጉባኤ ታገሴ ጫፎ እና ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ስራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።