አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያን ለማወክ በእብሪተኝነት የሚመጣ ማንኛውም ኃይል ኢትዮጵያ የአርበኞች ምድር መሆኗን ማስታወስ አለበት አሉ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን።
130ኛው የዓድዋ ድል በዓል “ከአኩሪ ታሪክ ወደ ብሩህ አድማስ” በሚል መሪ ሐሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል።
ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት÷ የዓድዋ ድል ዘመን ተሻጋሪ በዓል ነው፤ ለዚህ ድል ሚስጥሩ ደግሞ ጥልቅ የሀገር ፍቅር ነው ብለዋል።
የውጭ ወራሪ ኃይሎች ጭፍጨፋና በደል ቢፈጽሙብንም አልገዛም ባይ ኢትዮጵያዊያን ጀግኖች ወራሪዎችን አሳፍረውና አዋርደው በመሸኘት የሀገራቸውን ክብርና ነጻነት በማስጠበቃቸው ምስጋና ይገባቸዋል ነው ያሉት።
ትናንት በዓድዋ የተጎናጽፍነውን ድል ዛሬም በሌሎች ተግባሮቻችን ላይ በማስፋት የአያቶቻችንን አደራ ተቀብለን ኢትዮጵያን ወደ ታላቅ ከፍታ ማሸጋገር አለበን ሲሉም አጽንዖት ሰጥተዋል።
በሶስና አለማየሁ