ቢዝነስ

4ኛው የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ፎረም መጋቢት 17 እና 18 ይካሄዳል

By Hailemaryam Tegegn

March 03, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 4ኛው የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ፎረም የፊታችን መጋቢት 17 እና 18 በአዲስ አበባ ይካሄዳል ።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ፥ ፎረሙ ኢትዮጵያ ያላትን ምቹ የኢንቨስትመንት ምህዳር በስፋት የሚያሳይና የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የፈጠረውን ምቹ የኢንቨስትመንት እድል ለማስተዋወቅ የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡

“ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ዝግጁ ናት” በሚል መሪ ሃሳብ ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ፎረም ላይ ከ800 በላይ ዓለም አቀፍ ባለሀብቶች፣ የንግድ መሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች እንዲሁም የልማት አጋሮች አንደሚሳተፉ ጠቁመዋል፡፡

በ3ኛው የኢንቨስትመንት ፎረም ከ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር በላይ ስምምነቶች መደረጋቸውን አስታውሰው፥ በዚህ ዓመት ከትላልቅ ድርጅቶች ጋር ከ2 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር በላይ ስምምነቶች ለማድረግ ታቅዷል ነው ያሉት፡፡

ፎረሙን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከገንዘብ ሚኒስቴርና ከልማት አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር እንደሚያዘጋጀው ተገልጿል።

በቅድስት ብርሃኑ