አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ ኤክስፖርት-ኢምፖርት ባንክ (አፍሪኤግዚም) ቀጣናዊ እድገትን ለማፋጠን ለካሪቢያን ሀገራት የሚያቀርበውን ፋይናንስ ወደ 5 ቢሊየን ዶላር ከፍ አድርጓል፡፡
የባንኩ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ኢሎምቢ (ዶ/ር) በካሪቢያን ማህበረሰብ (ካሪኮም) የመሪዎች ጉባኤ ላይ እንዳሉት፥ አፍሪኤግዚም ባንክ ከካሪቢያን ማህበረሰብ ጋር ያለው ግንኙነት እያደገ ይገኛል፡፡
ባንኩ ለቀጣናው ሀገራት የሚያቀርበውን የገንዘብ ድጋፍ ከ3 ቢሊየን ዶላር ወደ 5 ቢሊየን ዶላር ማሳደጉን ገልጸው፥ በሚቀጥሉት ሶስትና አራት ዓመታት ውስጥ ገንዘቡን ሙሉ በሙሉ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡
አፍሪኤግዚም ባንክ በቀጣይ አስር ዓመታት ውስጥ በአግሮፕሮሰሲንግና በተፈጥሮ ሀብት ልማት ላይ ትኩረት በማድረግ የኢኮኖሚ መዋቅሩን ለማሻሻል ይሰራል ነው ያሉት፡፡
የስራ እድል ፈጠራ፣ የመንግስታትን የገቢ ስርዓት ማዘመንና ኢንቨስትመንትን ማሳደግ ባንኩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራባቸው ዘርፎች መሆናቸውን ገልጸው፥ ለካሪቢያን ማህበረሰብ የሚደረገው የፋይናንስ ድጋፍ መጨመር ወሳኝ ርምጃ ነው ብለዋል፡፡
የአቅም ግንባታና የንግድ ልውውጥን ለመደገፍ የፈጠራ ኢንዱስትሪዎችን ማጠናከር አንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡