አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሻዕቢያ ሥርዓት ዳግም ሕዝባችንን እንዲበድል እድል አንሰጠውም፤ ከሞከረ ደግሞ የመጨረሻው ሙከራ ነው የሚሆነው አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትግርኛ ቋንቋ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ላይ እንዳሉት፥ የሻዕቢያ ሥርዓት አለሁ ለማለት ብቅ ጥልቅ እያለ ነው።
የሻዕቢያ ሥርዓቱ በልማትና በሥልጣን ሽግግር እንደማያምን ገልጸው÷ ልጆቹንና የልጅ ልጆቹን ሳይቀር አያምናቸውም ብለዋል።
የሥራ ፍቅር ያለውና ሥራ ፈጣሪ የሆነው የኤርትራ ሕዝብ የሚሆነውን መንግሥት ማግኘት አለመቻሉን ተናግረዋል።
ሻዕቢያ ሥልጣን ሲይዝ ከ300 በላይ ፋብሪካዎች በኤርትራ የነበሩ ቢሆንም ዛሬ ሁሉም በሚባል ደረጃ መውደማቸውን ጠቅሰዋል።
ያኔ አስመራ ዩኒቨርሲቲ የምትባል አንድ ዩኒቨርሲቲ ነበረች፤ እሷም ተዘግታለች፤ ኤርትራ እንደ ሀገር አንድ ዩኒቨርሲቲ የላትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ የኤርትራ ሕዝብ ሀገሩን ትቶ ወደ ስደት አምርቷል ብለዋል።
በዚህም ሕዝቡ ኡጋንዳ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ወደ ሁሉም ሀገራት እየተሰደደ በመሆኑ ኤርትራ ባዶ እየሆነች መምጣቷን ገልጸዋል።
ከሀገራቸው የተሰደዱት በስደት ላይ ሠርተው እንዳይኖሩ ከእነርሱ ጋር ሰላዮችን ጭምር እየላከ ችግር ላይ እየጣላቸው መሆኑን አንስተው÷ ስደት ላይ ሆነውም ሰላም እያሳጣቸው ይገኛል፤ ይህ የክፋት ሁሉ መሰረት ነው ብለዋል።
እኛ ከልምዳችን የተማርነው ከዚህ ኃይል ምንም ጥሩ ነገር ማግኘት የማይታሰብ ነው በማለት ገልጸው÷ ዳግም ሕዝባችንን እንዲበድል እድል አንሰጠውም፤ ምናልባት ከሞከረ ደግሞ የመጨረሻ ሙከራ ነው የሚሆነው ሲሉም አስገንዝበዋል።
በዮናስ ጌትነት