ፋና ስብስብ

የመራጮች ምዝገባ ቦታ

By Adimasu Aragawu

March 04, 2026

 

1. የመራጮች ምዝገባ የሚከናወነው የመራጮችን መደበኛ መኖሪያ መሰረት በማድረግ በምርጫ ህጉ መሠረት በቦርዱ በሚቋቋም የምርጫ ጣቢያ ይሆናል፤

2. ከምርጫ ጣቢያ ውጪ ቤት ለቤትም ሆነ በተመሳሳይ ቦታ እየተዘዋወሩ የመራጮች ምዝገባ ማከናወን የተከለከለ ነው፤

3. ነገር ግን ቦርዱ በሚያወጣው መመሪያ መሠረት የአርብቶ አደሩን አኗኗር መሰረት ያደረገ ተንቀሳቃሽ የምርጫ ጣቢያ ሊያቋቁም ወይም ቤት ለቤት በመሄድ የመራጮች ምዝገባ እንዲከናወን ሊወስን ይችላል፤

4. የምርጫ ጣቢያዎች የአካል ጉዳተኞችን ልዩ ሁኔታ፣ ለመራጮች ምዝገባ እና ለሌሎች የምርጫ ተግባራት ምቹነታቸው፣ አማካይ እና መራጩ በቀላሉ ሊያውቃቸው የሚችሉ መሆናቸውን ጨምሮ የተለያዩ ታሳቢዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት ቦርዱ በሚወስነው ስፍራ በምርጫ አስፈጻሚዎች ተመቻችተው የሚቋቋሙ ይሆናል፤

5. የመራጮች ምዝገባ የሚከናወንበት ቦታ የመራጮች ምዝገባ ከመጀመሩ 15 ቀናት አስቀድሞ ለመራጩ ህዝብ እና ለተወዳዳሪዎች ይፋ መደረግ አለበት፤

6. በማንኛውም ምርጫ አንድ ምርጫ ጣቢያ የሚያስተናግደው የመራጮች ብዛት ከአንድ ሺህ አምስት መቶ መብለጥ የለበትም፤

7. ልዩ የምርጫ ጣቢያዎችን እንዲሁም ተንቀሳቃሽ የምርጫ ጣቢያዎችን በተመለከተ በምርጫ ሕጉና እነዚህን በሚመለከቱ መመሪያዎች ላይ የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ ለአንድ የምርጫ ጣቢያ በተከለለ አካባቢ ከአንድ የምርጫ ጣቢያ በላይ ማቋቋም አይቻልም፤

8. ነገር ግን በአንድ ምርጫ ጣቢያ ከአንድ ሺህ አምስት መቶ በላይ መራጮች የተገኙ እንደሆነ አዲስ የምርጫ ጣቢያ ተቋቁሞ የመራጮች ምዝገባው ይቀጥላል፡፡

9. ይህም ለልዩ የምርጫ ክልሎች በሚቋቋሙ እና በህግ በተለዩ ተቋማት በሚቋቋሙ ልዩ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ተፈጻሚ አይሆኑም፤

10. ቦርዱ ለምርጫው አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው የምርጫ ጣቢያ ቦታዎችን ሊለውጥ ይችላል፤ ለውጡንም ለመራጩ ህዝብ፣ ለተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ታዛቢዎች፤ የመራጮች ትምህርት ለሚሰጡ ሲቪክ ማህበራት እና ጋዜጠኞች ይፋ ማድረግ አለበት፡፡

11. ቦርዱ ይህንን የሚመለከት የአሰራር ስርዓት ሊዘረጋ ይችላል ፡፡

በምርጫ ብቻ! እርስዎ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ተዘጋጅተዋል