አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአቪዬሽን ዘርፍ የሰው ሀይል ልማት በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) በስምምነት ፊርማው ወቅት እንዳሉት፥ ዜጎችን ከሀገር ውስጥ ባሻገር በውጭ ሀገራት የሥራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል።
ስምምነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአቪዬሽን ዘርፉ በቴክኖሎጂ እና በሰው ሀይል ልማት ያለውን የዳበረ ልምድ በስልጠና በማስፋት ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት ያስችላል ነው ያሉት።
ለዚህም በሚኒስቴሩ ስር በሚገኙ የሙያና ስልጠና ተቋማት አማካኝነት የአቪዬሺን ባለሙያዎችን በማፍራት በሀገር ውስጥ እና በውጭ የሥራ እድል ለመፍጠር የሚያግዝ መሆኑንም ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ የአቪዬሺን ዘርፉ በርካታ ሙያተኞችን እንደሚፈልግ የተገለጸ ሲሆን፥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ ባለሙያዎችን ለማፍራት የተቋማቱ ስምምነት ወሳኝ መሆኑ ተመላክቷል።
አየር መንገዱ በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ የሥራ እድሎችን የሚፈጥር ሲሆን፥ ከሚኒስቴሩ ጋር የተደረሰው ስምምነት የበቁ ባለሙያዎችን እንዲያገኝ ያስችለዋል ነው የተባለው።
በኃይለማርያም ተገኝ