ጤና

በኦሮሚያ ክልል የእናቶች እና ህጻናት ጤና ለመጠበቅ የሚሰራው ስራ ውጤት እያመጣ ነው

By abel neway

March 04, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል የእናቶች እና ህጻናት ጤና ለመጠበቅ የሚሰራው ስራ ከፍተኛ ውጤት እያመጣ ነው አለ የክልሉ ጤና ቢሮ።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ነጻነት ወርቅነህ (ፕ/ር) በክልሉ ጅማ ዞን ሸቤ ሶምቦ ወረዳ የእናቶች እና ህፃናትን ጤና ለመጠበቅ እየተደረገ ያለውን ጥረት ተመልክተዋል።

ነጻነት ወርቅነህ (ፕ/ር) ከምልከታው በኋላ በሰጡት አስተያየት፤ እንደ ክልል የእናቶች እና የህጻናት ሞትን ለመቀነስ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዚህም ስለ እናቶች እና ህጻናት ጤና ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ የአቅም ግንባታ እንዲሁም ተቋማትን በግብዓት ማሟላትና ደም ማሰባሰብ ላይ በስፋት መሰራቱን ተናግረዋል።

ጤናማ የእርግዝና፣ ወሊድና ድህረ ወሊድ አገልግሎቶችን ለሁሉም እናቶች ተደራሽ እንዲሆን የተጀመረው ጥረት መጠናከር እንዳለበት ገልጸው፤ ለእናቶች እና ህጻናት ጤና ትኩረት በመስጠት ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ ይገኛል ነው ያሉት።

የተሰራዉ ስራ ከፍተኛ ውጤት ማምጣቱን ጠቅሰው፤ ለላቀ ስኬት የመድሀኒት አቅርቦት፣ የጨቅላ ህጻናት ማቆያን ጨምሮ ሌሎችም አገልግሎቶች በተሟላ መንገድ ለማዳረስ ከህብረተሰቡ እና ከአጋሮች ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሆነ አመልክተዋል።

በበሪሳ ኃ/ማርያም