ፋና ስብስብ

በመራጭነት ለመመዝገብ የሚቀርቡ ማስረጃዎች፡-

By Adimasu Aragawu

March 05, 2026

ሀ) ማንነትን የሚገልፅ የቀበሌ መታወቂያ ካርድ ወይም ፓስፖርት፣

ለ) የቀበሌ መታወቂያ ካርዱ ወይም ፓስፖርቱ ያልታደሰ ቢሆንም እንኳን ለምዝገባ ሊያገለግል ይችላል፡፡ ነገር ግን የካርዱ ዕድሳት ጊዜ ከአምስት አመት በላይ ያለፈው ከሆነ ሌላ ማረጋገጫ ማቅረብ ይጠበቃል፡፡

ሐ) የቀበሌ መታወቂያ ካርድ ወይም ፓስፖርት ማቅረብ ካልተቻለ የቅርብ ፎቶግራፍ ተደርጎበት የተሰጠ እንደ መንጃ ፈቃድ፣ የመኖሪያ የምስክር ወረቀት፣ ከውትድርና የተገለሉበት ሰነድ፣ የትምህርት ቤት መታወቂያ፣ የሰራተኛነት መታወቂያ የመሳሰሉ የመለያ ማስረጃዎች በመራጭነት ለመመዝገብ የሚያስችሉ ሰነዶች ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡

👉 ነገር ግን ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ማስረጃዎች በማይኖሩበት ወቅት፡-

ሀ) ከምርጫ አስፈጻሚዎቹ ሁለቱ መራጩን ለይተው የሚያውቁ ከሆነ በአስፈጻሚዎቹ ምስክርነት ወይም፣

ለ) በገጠር አካባቢ ሲሆን በባሕላዊና በልማዳዊ ዘዴ ተመዝጋቢውን ለመለየት የሚቻልበት ሁኔታ ካለ ባሕሉን የሚያውቁ ሁለት ሰዎች ለምርጫ ጣቢያው ሰብሳቢ በሚሰጡት ምስክርነት ቃለ ጉባኤ ተይዞ እና በቃለ ጉባዔው ላይ የምርጫ ጣቢያው አስፈጻሚዎች ተፈራርመውበት ምዝገባው ይከናወናል፡፡

ሐ) የተመዝጋቢ እድሜ 18 ዓመት ስለመሆኑ የሚቀርብ ማስረጃ ሳይኖርና ወይም ጥርጣሬ ሲኖር በተመዝጋቢ ቤተሰብ አንጋፋ አባል ወይም ዘመድ፣ እነሱ ከሌሉ ስለግለሰቡ የሚያውቁ ሁለት ሰዎች ለምርጫ ጣቢያው ሰብሳቢ በሚሰጡት የምስክርነት ቃል በማረጋገጥ ሂደቱ በቃለ ጉባዔ ተይዞ ሊመዘገብ ይችላል፡፡

መ) የሚሰጠውን ምስክርነት የምርጫ ጣቢያው ሃላፊ ይሰማል፤ በቃለ ጉባዔው ላይ የምርጫ ጣቢያው አስፈጻሚዎች ይፈራረሙበታል፡፡

የምርጫ ጣቢያው በተቋቋመበት ቀበሌ ለረዥም ጊዜ በመደበኛነት መኖራቸው በሰነድ የተረጋገጠ ሦስት ግለሰቦች በሚሰጡት ምስክርነት የሰነድ ማስረጃ አልባውን ተመዝጋቢ ለመለየት ከተቻለ ሂደቱ ቦርዱ በሚያዘጋጀው የቃለ ጉባዔ ላይ የምርጫ ጣቢያው አስፈጻሚዎች ተፈራርመውበት ምዝገባው ሊከናወን ይችላል፡፡

👉 ስለመራጭ ማንነት፣ ነዋሪነት ወይም ሌላ ሁኔታ ማንኛውም ዓይነት ምሥክርነት የሚሰጥ ሰው፡-

ሀ) በመራጭነት የተመዘገበ፣

ለ) እጩ ተወዳዳሪ ወይም የእጩ ተወካይ ያልሆነ መሆን ይኖርበታል፡፡

👉 ከላይ ከተመለከቱት ማረጋገጫዎች በአንዱ ብቻ የመራጩን ማንነትና የነዋሪነት ቆይታ ማረጋገጥ ያልተቻለ እንደሆነ መዝጋቢዎች ከአንድ በላይ መስፈርቶችን በመጠቀም ያረጋግጣሉ፡፡