ጤና

የዲቦራ ፋውንዴሽን ማስተባበሪያ ቢሮ በቡታጅራ ጠቅላላ ሆስፒታል ተከፈተ

By Adimasu Aragawu

March 05, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዲቦራ ፋውንዴሽን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመጀመሪያ ቅርንጫፍ ማስተባበሪያ ቢሮ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምስራቅ ጉራጌ ዞን ቡታጅራ ጠቅላላ ሆስፒታል ላይ ከፍቷል።

የፋውንዴሽኑ መስራችና ባለቤት አቶ አባዱላ ገመዳ ምስረታውን አስመልክቶ እንደገለጹት÷ የዳውን ሲንድረም የድጋፍና አገልግሎት ማዕከል ለሁሉም መድረስ ባይቻልም ለሌሎች መነቃቃትን በመፍጠርና እየተስፋፋ የመጣውን ይህን ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍና መንገድ ለማመላከት ያለመ ነው።

በቡታጅራ ማዕከል ውስጥ የፊዝዮቴራፒ፣ የሳይኮ ቴራፔ እንዲሁም የባህሪ ቴራፒ ስልጠና እንደሚጀመር ገልጸው÷ ሁሉም ትምህርት ቤት ውስጥ የዳውን ሲንድረም ተጠቂ ህፃናትን ተቀብሎ እንዲያስተምሩ ለማድረግ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እንደሚሰራ አንስተዋል።

ቅርንጫፍ ቢሮውን ለሌሎች አርዓያ ሊሆን በሚችል መልኩ በማስፋፋት የመማሪያ ትምህርት ቤት በመክፈት፣ በቂ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙና የተሻለ አገልግሎቶችን በመስጠት ውጤታማ ማዕከል ለማድረግ በትኩረት እንሰራለን ብለዋል።

በተፈጥሮ ችግር የተወለዱት ህፃናትን ተደብቀዉ ቤት እንዳይቀሩ የግንዛቤ ስራዎችን ማስፋፋት ይገባልም ነው ያሉት።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ በበኩላቸው÷ የዳውን ሲንድረም ተጠቂ ህፃናት መጠናቸው ከፍተኛ በመሆኑ እናቶችና ህፃናትን ለመርዳት በክልሉ የመጀመሪያ የሆነውን የዲቦራ ፋውንዴሽን ማዕከል መከፈቱን ጠቅሰዋል።

በክልሉ በተፈጥሮ የአፈጣጠር ችግር ያለባቸው ህፃናት የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ልዩ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ለሀገር ተሞክሮ ሊሆን የሚችሉ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመዋል።

የዲቦራ ፋውንዴሽን ማዕከል በክልሉ በመክፈት ሰብዓዊ ኃላፊነታቸውን ለተወጡ ለፋውንዴሽኑ መስራች አባዱላ ገመዳ ምስጋና ማቅረባቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ ሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ቢኒያም ገዙ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል።