ቢዝነስ

ኢትዮ ቴሌኮምና ኤሪክሰን ዲጂታል መሰረተ ልማትን ለማጠናከር ተፈራረሙ

By Hailemaryam Tegegn

March 05, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም የኔትዎርክ ማስፋፊያን በማከናወንና በማዘመን የዲጂታል መሰረተ ልማትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችለውን ስምምነት ከኤሪክሰን ኩባንያ ጋር ተፈራርሟል፡፡

ስምምነቱ በባርሴሎና እየተካሄደ ከሚገኘው የዓለም አቀፍ የሞባይል ኮንግረስ ጎን ለጎን የተፈረመ ሲሆን፥ በኔትዎርክ ኩባንያው ቀጣና በሚገኙ 1ሺህ 500 የሞባይል ጣቢያዎች ላይ የማስፋፊያ፣ የማሻሻያና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የመገንባት ስራዎችን ያካትታል።

ከኢትዮ ቴሌኮም የሦስት ዓመት ስትራቴጂ ጋር የተጣጣመው ስምምነቱ የኔትዎርክ ሽፋንን፣ ጥራትንና አቅምን በከፍተኛ ሁኔታ በማሻሻል ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ የሚያስፈልገውን ፈጣን አገልግሎት ለማቅረብ ያስችላል ነው የተባለው፡፡

በተጨማሪም ከከተሞች ባሻገር 75 ለሚሆኑ የገጠር አካባቢዎች ተስማሚ የሆኑ የሞባይል ቴክኖሎጂ አገልግሎቶችን ለማቅረብ የሚያስችል ሲሆን፥ የኤልቲኢ አገልግሎት ተደራሽነትን ወደ 276 ከተሞች እንደሚያሳድግ ይጠበቃል፡፡

ስምምነቱ እንደ ቴሌብር፣ ዘመን ገበያ እና ዘኔክሰስ ለመሳሰሉ ሀገራዊ ፕላትፎርሞችን በመደገፍ በሀገራችን እያደገ ለመጣው የዲጂታል ሥነምህዳር ጠንካራ መሠረት እንደሚሆን ኢትዮ ቴሌኮም አስታውቋል፡፡