ቢዝነስ

የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ “ንዋይ” የተሰኘ የሞባይል መተግበሪያ ይፋ አደረገ

By Adimasu Aragawu

March 05, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ የካፒታል ገበያን ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል “ንዋይ” የተሰኘ የሞባይል ግብይት መተግበሪያ በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጓል።

መተግበሪያው በሀገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ማንኛውም ግለሰብ ሞባይል ስልኩን በመጠቀም በአክሲዮን እና በዕዳ ሰነዶች ግብይት ላይ በቀጥታ እንዲሳተፍ እድል የሚሰጥ ነው።

የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ዋና ስራ አስፈፃሚ ጥላሁን እስማኤል (ዶ/ር) በመተግበሪያው የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ እንዳሉት÷ “ንዋይ” ገበያውን በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እጅ ላይ ተደራሽ ያደርገዋል።

መተግበሪያው ባለሀብቶች በማንኛውም ጊዜና ቦታ ሆነው በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ በቀጥታ እንዲሳተፉ የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው÷ የሰነድ ግዢና ሽያጭ ትዕዛዞችን በስልክ ማስተላለፍና መፈጸም እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀና ተልኽቁ በበኩላቸው÷ በርካታ ሀገራት ወደዚህ ዓይነት የቴክኖሎጂ ሥርዓት ለመድረስ ረጅም ጊዜ እንደወሰደባቸው አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ ግን ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ በመማር በአጭር ጊዜ ውስጥ ዘመናዊ የገበያ ሥርዓት መገንባቷን አስረድተዋል።

በሁሉም የሀገሪቱ ጫፍ ያሉ ዜጎች የኢንቨስትመንት አካውንት በመክፈት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው ግልጽና ተገማች የሆኑ ህጎች መውጣታቸው ለዚህ ስኬት ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ሥራ አስፈጸሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) ገበያው ሁሉም ዜጋ በአቅሙ ልክ የሚሳተፍበት መሆኑን አጽንኦት በመስጠት÷ እንደ ቴሌ ብርና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መተግበሪያዎች ያስመዘገቡት ስኬት ለ”ንዋይ” ውጤታማነት እንደ ማሳያ እንደሚጠቀስ ገልጸዋል።

መተግበሪያውን በአሁኑ ወቅት በአንድሮይድ እና በአይኦኤስ ስልኮች ላይ ለመጫን ዝግጁ መሆኑን ጠቅሰው÷ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ የካፒታል ገበያ ባለቤት የማድረግ ግብን ለማሳካት እየተሰራ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።