የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ በፈተናዎች ጸንታ የቆመችው በሠራዊታችን ተጋድሎ ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

By Mikias Ayele

March 06, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በፈተናዎች ጸንታ የቆመችው በማይበገረው የሠራዊታችን ተጋድሎ ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጃንሜዳ አካባቢ በቅርቡ የተመረቀውን የመከላከያ ሠራዊት ሙዚየም ከጎበኙ በኋላ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሙዚየም የጀግንነታችን ማኅደር፣ የልዕልናችን ምስክር ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በታሪኳ በፈተናዎች ጸንታ የቆመችው በማይበገረው የሠራዊታችን ተጋድሎ ነው በማለት ገልጸው÷ ሙዚየሙ ይህንን የዘመናት የጀግንነት ጉዞ የሚመሰክሩ ህያው አሻራዎችን መያዙን አንስተዋል፡፡

ከ1950ዎቹ ጀምሮ እንዲቋቋም ሲታለም የቆየው ይህ የጦር ሙዚየም በፖለቲካዊ ውሳኔዎች ምክንያት ሲጓተት ቆይቶ በለውጡ መንግሥት ቁርጠኝነት ተቋማዊ ቁመና ተላብሶ እውን መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ይህ ስኬት ለሚገነባው ግዙፍ ብሔራዊ የሰራዊት ሙዚየም እንደ ማዕዘን ድንጋይ የሚወሰድ መሆኑም ነው ያስገነዘቡት፡፡

በሙዚየሙ የሚገኙት እና ከዓድዋ ዘመን በፊት የነበሩ ብርቅዬ መሳሪያዎች፣ የነገሥታቱ ትጥቆችን እና በሙዚየሙ ያሉት የጦር ታሪክና ቅርሶች የቀደምት ጀግኖችን ታሪክ እንደሚዘክሩ ገልጸዋል፡፡

ከ1900 ጀምሮ ያለውን ዘመናዊ የተቋም ግንባታ፣ የጦር መሣሪያዎች ዝግመተ ለውጥና መከላከያ የደረሰበትን አስደናቂ የምህንድስና ጉዞ የሚያስቃኘው ይህ ማዕከል ለሠራዊቱና ለትውልድ ታሪክን፣ ዕውቀትንና መነሳሳትን የሚያስታጥቅ ነው ብለዋል።

በሙዚየሙ ከትናንቱ እንማርበታለን፤ ዛሬን እንገመግምበታለን፤ ለነገ ደግሞ እናቅድበታለን ሲሉ ገልፀው÷ አፍሪካውያንና መላው በፀረ ቅኝ አገዛዝ የታገለ የዓለም ሕዝብ ሁሉ ሙዚየሙን እንዲጎበኝ ጋብዘዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሠራዊት ከሀገር አልፎ በዓለም ስሙ ከፍ ብሎ የሚነሳ የሰላም ዘብ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሠራዊቱ ገድል ለትውልድ እንዲሸጋገር መንግሥት አስፈላጊ ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡