አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከተመዘገቡ 47 ፓርቲዎች 10 ሺህ 934 እጩዎች በምርጫ ለመወዳደር ቀርበዋል አለ፡፡
የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ÷ ከነገ የካቲት 28 ጀምሮ ለአንድ ወር የሚቆይ የመራጮች ምዝገባ ይካሄዳል፡፡
በምዝገባ ሂደቱ 18 ዓመት የሞላው ኢትዮጵያዊ፣ በአካባቢው 6 ወር የኖረና በልዩ ሁኔታ ምርጫ ያልተከለከለ ዜጋ ሁሉ መሳተፍ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
ከየካቲት 28 ጀምሮ እስከ መጋቢት 1 ቀን ድረስ ሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች የሚከፈቱ ሲሆን ምዝገባውን ለማካሄድ ምርጫ ቦርድ በሁሉም ጣቢያዎች ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልፀዋል፡፡
በቦርዱ ከተመዘገቡ 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች 10 ሺህ 934 እጩዎች መቅረባቸውን ገልጸው÷ 2 ሺህ 98 ዕጩዎች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲሆኑ 8 ሺህ 736 ደግሞ የክልል ተዋካዮች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
በግል ለመወዳደር 73 እጩዎች መመዘገባቸውን ተናግረዋል፡፡
ቦርዱ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የሚቀየር የምርጫ ክልልን፣ የሚቀየር የክልል ምክር ቤት እና የተወካዮችን መቀያየር በመነጋገር አጽድቆ መጨረሱንም ነው ያሰገነዘቡት፡፡
ፓርቲዎች የሚወዳደሩበትን የምርጫ ዕጣ ሥነ-ሥርዓት ቦርዱ እንደሚወስን ጠቁመው፤ የምርጫ አስቻይ ሁኔታዎችን በአረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ የመለየት ሥራ ከፓርቲዎች ጋር በመሆን እየተሠራ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
በአምደወርቅ ሽባባው