አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሠራዊት ሙዚዬም ለሀገር ግንባታ ዝግጁ የሆነ ትውልድ ለመቅረጽ ያስችላል አሉ የመከላከያ ሙዚዬምና ቅርስ ጥናት አስተዳደር ዳይሬክተር ሜ/ጄነራል ጥሩዬ አሰፌ።
ሜ/ጄ ጥሩዬ አሰፌ እንዳሉት÷ የኢትዮጵያ ሠራዊት ሙዚዬም ከአክሱም ዘመነ መንግሥት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያሉ የኢትዮጵያ ወታደራዊ ታሪኮች እና ቅርሶች በዝርዝር ሰንዶ የያዘ ነው።
ከለውጡ በኋላ መንግሥት ለታሪክና ለቅርስ ባሳየው ቁርጠኝነት ሙዚዬሙ በዘመናዊ መልኩ እንደ አዲስ መገንባቱንና የሠራዊቱን ጀግንነት የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በሙዚዬሙ በዓድዋ ጦርነት ወቅት ጀግኖች አባቶች የተጠቀሙባቸው መሣሪያዎችና የሀገርን ዳር ድንበር ለማስከበር የተከፈሉ መስዋዕትነቶችን የሚያሳዩ ተጨባጭ ማስረጃዎች እንደሚገኙበት አስረድተዋል።
የሙዚዬሙ መገንባት ትውልዱ የሀገሩን ታሪክ በቀላሉ እንዲረዳ እንደሚስችል ጠቁመው÷ ኢትዮጵያ በታሪኳ ሁሉ ሉዓላዊነቷን በተግባር ማረጋገጧን በግልጽ የሚያሳይ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በትናንትናው ዕለት በቅርቡ የተመረቀውን የመከላከያ ሠራዊት ሙዚዬም መጎብኘታቸው ይታወሳል፡፡