የሀገር ውስጥ ዜና

ሚሊየኖች እውቀትና ምግብም የሚመገቡበት ትውልድ ተኮር ልማት በመዲናዋ…

By abel neway

March 07, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የተማሪዎች ምገባ አገልግሎት 1 ሚሊየን ገደማ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል አለ የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ።

የቢሮው ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) ለፋና ዲጂታል እንደገለጹት፥ በከተማ አስተዳደሩ ለትምህርት ዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት በተሰሩ ስራዎች አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡

የተማሪዎችን ውጤት ማሻሻልና በወላጆች ላይ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ጫና መቀነስን ታሳቢ ባደረገው የተማሪዎች ምገባ በሁሉም የትምህርት ተቋማት ከቅድመ አንደኛ እስከ 8ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎችን በቀን ሁለት ጊዜ መመገብ መቻሉን ገልጸዋል።

መርሐ ግብሩ በ2012 የትምህርት ዘመን 300 ሺህ ተማሪዎችን በመያዝ መጀመሩን አስታውሰው፥ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን 1 ሚሊየን ገደማ ተማሪዎችን መመገብ ተችሏል ብለዋል።

የምገባ አግልግሎቱ የተማሪዎችን የትምህርት አቀባበል በማሻሻል እንዲሁም ትምህርት የማቋረጥና የመድገም ምጣኔን በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አስረድተዋል።

ለአብነትም በ2009 የትምህርት ዘመን 1 ነጥብ 4 በመቶ የነበረው የትምህርት ማቋረጥ ምጣኔ በ2017 ወደ 0 ነጥብ 3 በመቶ መቀነሱን አመልክተዋል።

የተማሪዎች ምገባ መርሐ ግብር የወላጆችን የኢኮኖሚ ጫና በሚታይ መልኩ መቀነሱን ገልጸው ፥ ከ16 ሺህ በላይ የተማሪ ወላጆች በምገባ ማህበራት እንዲደራጁ በማድረግ የስራ እድል ተፈጥሮላቸዋል ነው ያሉት።

የከተማ አስተዳደሩ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥና ለሀገር ተረካቢ ትውልድ ግንባታ ትኩረት በመስጠት በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ነው ያሉት ሃላፊው ÷በዚህም አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

ከትምህርት ቤት ምገባ በተጨማሪ በትምህርት ዘመኑ በከተማዋ በሁሉም የመንግሥት ት/ቤቶች ለሚማሩ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስና የደንብ ልብስ ማቅረብ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ