አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓለም ገበያ ተሳትፎን ለማሳደግ ላኪዎች ምርትን መከዘን አቁመው በወቅቱ ለገበያ ሊያቀርቡ ይገባል አሉ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)፡፡
ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) የ2018 በጀት ዓመት የወጪ ንግድ አፈጻጸምና ቀጣይ የክንውን አቅጣጫዎች በተመለከተ ከላኪዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡
ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ በበጀት ዓመቱ ባለፉት ሰባት ወራት ከወጪ ንግድ 5 ነጥብ 91 ቢሊየን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡
አፈጻጸሙ የዕቅዱ 117 በመቶ መሆኑን ገልጸው ÷ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ65 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን አመልክተዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ለማሳካት ከታቀደው 9 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር በላይ ለመፈጸም ከባለድርሻ አካላት ጋር ከፍተኛ ርብርብ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
የወጪ ንግድ ኮንትራት ምዝገባና የመላኪያ ፈቃድ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ወደ ኦንላይን ሥርዓት መሸጋገሩ ላኪዎች የትም ሆነው ሥራቸውን እንዲያቀላጥፋ እንዳስቻላቸው አረጋግጠዋል፡፡
ላኪዎች ምርትን መከዘን አቁመው በወቅቱ ወደ ገበያ በማውጣት በዓለም አቀፍ ገበያ የሚገባንን ሀገራዊ ፋይዳ እንዲያስጠብቁ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
በቀጣይ የኢትዮጵያን ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ በሚገባ ለማስተዋወቅ በትኩረት መስራት እንደሚገባ በመድረኩ ተመላክቷል፡፡
በመላኩ ገድፍ