አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ከመጋቢት 6 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ታላቅ ሀገራዊ የገቢ ማሰባሰቢያ ንቅናቄ ያካሂዳል።
የማዕከሉ የገቢ ማሰባሰቢያ ንቅናቄ አስተባባሪ ኮሚቴ የገቢ አሰባሰብን አስመልክቶ በዛሬው ዕለት መግለጫ ሰጥቷል።
የመቄዶንያ መስራች ቢኒያም በለጠ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ከዚህ በፊት በተካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ተሰብስቧል።
ከመጋቢት 6 ጀምሮ በሚካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ ንቅናቄ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ዜጎች በገንዘብ፣ በእውቀትና በሌሎች ቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ሕብረተሰቡም በ7979 ላይ በሁሉም ባንኮች ድጋፍ ማድረግ እንደሚችል ገልጸው÷ ማዕከሉ ቋሚ ገቢ ስለሌለው በተለይም በውጭ የሚኖሩ ዜጎች እንዲሳተፉ ጠይቀዋል።
የገቢ ማሰባሰቢያ ንቅናቄው በዩቲዩብ በቀጥታ ስርጭት እንደሚከናወንም ተናግረዋል።
የመቄዶንያ የገቢ ማሰባሰቢያ ንቅናቄ አስተባባሪ ጋዜጠኛ በፍቃዱ አባይ በበኩሉ÷ የተጀመረው የህክምና መስጫ ሆስፒታል ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት እንዲችል እስከ መጨረሻው የገቢ ማሰባሰቢያ ንቅናቄ ቀን ድረስ በትብብር መስራት አስፈላጊ መሆኑን አንስቷል።
ማዕከሉ የጀመረውን ሰብዓዊ አገልግሎት አጠናክሮ እንዲቀጥል ሁሉም ዜጋ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል።
ከመጋቢት 6 ጀምሮ በሚካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ ንቅናቄ የሚገኘው ገቢ አዲስ አበባ ላይ የተጀመረውን ባለ15 ወለል ህንፃ እና በክልል ከተሞች ላይ በሚገኙ 15 ቅርንጫፎች ላይ የተጀመሩ ግንባታዎችን ለማጠናቀቅ እንደሚውል ተገልጿል።
በተጨማሪም በማዕከሉ የሚረዱ ወገኖችን ቁጥር ለመጨመርና የተሻለ የኑሮ ሁኔታ ለመፍጠርም ያለመ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን÷ ለስኬቱ የሚዲያ አካላት፣ የማሕበራዊ ሚዲያ አንቂዎችና ታዋቂ ሰዎች ማዕከሉን በማስተዋወቅ እንዲያግዙ ጥሪ ቀርቧል።
በየሻምበል ምህረት