አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሴቶች በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የብልፅግና እና የእኩልነት ጉዞ ላይ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እያበረከቱ ነው አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ115ኛ እንዲሁም በኢትዮጵያ ለ50ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ እና የስፖርት ውድድር መካሄዱን ገልፀዋል፡፡
ከቦሌ ተርሚናል – አትላስ – ኡራኤል በተገነባው የኮሪደር መስመር ተጀምሮ እስከ ሴቶች አደባባይ በዘለቀው የሩጫ ውድድር ላይ ከ120 ሺህ በላይ የሚሆኑ የከተማዋ ሴቶች፣ ታዋቂ አትሌቶች እና የውጭ ሀገራት ዜጎች መሳተፋቸውን ጠቁመዋል፡፡
አሁን ላይ ሴቶች በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የብልፅግና እና የእኩልነት ጉዞ ላይ በንቃት በመሳተፍ፣ ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጡ እና የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛሉ ብለዋል።
ይህ ሁለንተናዊ ተሳትፎ እና እኩል ተጠቃሚነት በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚጥልም ከንቲባዋ አረጋግጠዋል፡፡