አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ብሔራዊ ጥቅምን ለታሪካዊ ጠላቶች አሳልፎ ለመስጠት የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች በኢትዮጵያ ፖለቲካ አውድ ውስጥ ባለድርሻ ሊሆኑ አይገባም አሉ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀ መንበር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)።
ቀይ ባህር ያለ ኢትዮጵያ ህዝብ ፈቃድና ይሁንታ በፖለቲካ ሴራ ያጣነው የተፈጥሮ ሃብታችን ነው ያሉት ሊቀመንበሩ፥ ምንም ዓይነት ህጋዊ መሰረት በሌለው አግባብ እንድናጣ መደረጉ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመ ታላቅ በደል መሆኑን አንስተዋል።
ይህንን ታሪካዊ ሀብት ማጣት በአሁኑ ትውልድ ዘንድ ከፍተኛ የቁጭት ስሜት መፍጠሩን ገልጸው፥ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄው የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊ፣ ህጋዊና መልክዓምድራዊ መብት መሰረት ያደረገ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
መንግስት ይህን የህዝብ ጥያቄ ለመመለስና የኢትዮጵያን ስትራቴጂያዊ ጥቅም ለማስከበር በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ረዥም ርቀት መጓዙን አስታውሰው፥ ጥያቄው ሀገራዊ አጀንዳ መደረጉን ፓርቲያቸው በአዎንታ እንደሚቀበለውና እንደሚደግፈው አረጋግጠዋል፡፡
ኢትዮጵያ በታሪክና በተፈጥሮ ያላትን የባህር በር የማግኘት መብት ዳግም የሚያረጋግጥላት ምቹ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚገባ የገለጹት ሊቀመንበሩ፥ አብን ይህንን ፍትሃዊ ጥያቄ ከግብ ለማድረስ በቁርጠኝነት ይሰራል ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለታሪካዊ ጠላቶች አሳልፈው ለመስጠት የሚሰሩ የፖለቲካ ኃይሎች በፖለቲካው አውድ ውስጥ ባለድርሻ አካል መሆን እንደሌለባቸው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የዓባይ ውሃ ለኤሌትሪክ ሃይል ማመንጫነት በመገደብ ተጠቃሚነቷን በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ማረጋገጧን አንስተው፥ የባህር በር ጥያቄ ላይም በጋራ መስራት እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
ታሪካዊ ጠላቶች ኢትዮጵያ የልማት ጥረቶቿ እንዲደናቀፉ ሌት ተቀን እንደሚሰሩ ያመለከቱት ሊቀመንበሩ፥ ኢትዮጵያውያን ግን የጋራ ጠላቶቻቸውን ሴራ በፅናት የመከቱበት ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
አሁን ላይ ከእነዚህ የብሔራዊ ጥቅም ጉዳዮች በላይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ሌላ ምንም ዓይነት አጀንዳ እንደሌለ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡