አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በድሬዳዋ ከተማ ተስፋ ሰጪ የልማት ስራዎች ተከናውነዋል አሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በድሬዳዋ ከተማ የልማት ዕቅዶችን አፈጻጸም ለመገምገም ያደረጉትን ጉብኝት አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ባለፈው ዓመት በከተማዋ በነበራቸው ቆይታ በከተማዋ በርካታ የልማት እቅዶችን አስቀምጠው እንደነበር አስታውሰው፥ በዚህ ጉብኝታቸው በድሬዳዋ ተስፋ ሰጪ የከተማ ልማት እንቅስቃሴዎችን ተመልክቻለሁ ብለዋል፡፡
በከተማዋ በርካታ መሰረተ ልማቶች መገንባታቸውን ገልጸው፥ ለአብነትም አዲስ አበባ ከሚገኘው አብርሆት ቤተ መጻሕፍት ጋር ተመሳሳይነት ያለው እመርታ ቤተመጻሕፍት የከተማዋ ድምቀት ሆኖ መገንባቱን ጠቅሰዋል፡፡
ቤተመጻሕፍቱ ከመደመር ትውልድ መፅሐፍ ሽያጭ በተገኘ ገቢ የተገነባ ሲሆን፥ ለከተማዋ ወጣቶች የእውቀት መገበያያና የአዕምሮ ማጎልበቻ እየሆነ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በከተማዋ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች ለታዳጊ ለወጣቶች የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች፣ የመዝናኛ ስፍራዎች፣ ፓርኮች፣ የሳይክል መንገዶችና ሌሎች በርካታ መሰረተ ልማቶች መገንባታቸውን አብራርተዋል፡፡
በድሬዳዋ የኮሪደር ልማት ነባርና አዳዲሶቹን ጨምሮ 187 ኪሎ ሜትር መንገድ ተገንብቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በከተማዋ ለውጥና እምርታ እንዳለ መመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡
እነዚህ እምርታዎችን በአገልግሎት ሰጭ ተቋማት፣ በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትና በሌሎች መስኮች ማጠናከር እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት፡፡
በተጨማሪም ለከተማዋ የስራ እድል የሚፈጥሩና ገቢን የሚያሳድጉ ሆቴሎችን፣ ሬስቶራንቶችንና ሌሎች የንግድ ተቋማትን ማስፋፋት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ