ፋና ስብስብ

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ፋውንዴሽን ለተለያዩ አካላት ከ750 ሺህ ብር በላይ የሚገመቱ ማሕበራዊ ድጋፎችን አደረገ

By Adimasu Aragawu

March 10, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ፋውንዴሽን በአማራ ክልል ባሕር ዳር እና ጎንደር ከተሞች ለተለያዩ አካላት ከ750 ሺህ ብር በላይ የሚገመቱ ማሕበራዊ ድጋፎችን አድርጓል።

ፋውንዴሽኑ በባሕር ዳር ከተማ ለሕዝብ ቤተ መጻሕፍት ከ300 ሺህ ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው 680 ማጣቀሻ መጻሕፍት፣ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው 100 ቤተሰብ 200 ሺህ ብር የሚገመቱ የጤና መድህን ክፍያ እንዲሁም ከ3 ሺህ 900 በላይ ህፃናትና አረጋውያንን ለሚረዳው ዝግባ የህፃናት እና አረጋውያን መርጃ ማዕከል የ250 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጉ ተመላክቷል።

በርክክቡ ወቅት የተገኙት የባሕርዳር ከተማ ባህል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ ጋሻው እንዳለው ፋውንዴሽኑ ለማሕበረሰብ ልማት ቁልፍ የሆነው የንባብ ባህል እንዲዳብር የማጣቀሻ መጻሕፍት ድጋፍ በማድረጉ ለባሕርዳር ያለውን ፍቅር አሳይቶናል ብለዋል።

የከተማዋ ጤና መምሪያ ኃላፊ ሲስተር ዓለም አሰፋ በበኩላቸው÷ ማህበረሰቡ ህመም ሲያጋጥመው በምን ገንዘብ ልታከም እንዳይል ተቋሙ ያደረገው የጤና መድህን ድጋፍ ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳለው ተናግረዋል።

የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ፋውንዴሽን በበጀት ዓመቱ ለሁሉም ክልሎች አንድ አንድ ሚሊየን ብር በመመደብ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች የጤና መድህን መዋጮ ከፍሏል ያሉት የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ጥላሁን ብርሃኑ ናቸው።

በጎንደር ከተማ ለ100 አባዎራና እማዎራዎች የጤና መድህን መዋጮ ሸፍኗል ያሉት ኃላፊው÷ የተደረገው ድጋፍ የማሕበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ማግኘት ላልቻሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች የጤና ዋስትና የሰጠ ነው ብለዋል።

መሠል ድጋፎችና የኢፍጣር ፕሮግራም በቀጣይ እንደሚኖር ገልጸው÷ የጤና መድህን ወጪው በቀጣይ ዓመታትም ለተጠቃሚዎቹ እንደሚሸፈን ተናግረዋል።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ ኃላፊ ሰይድ የሻው ለተደረገው ድጋፍ በማመስገን የግሉ ዘርፍ መሰል ማሕበራዊ ኃላፊነቶቹን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

በላይነህ ዘለዓለም