አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ረጅሙ የሰው ልጆች የሕልውና ታሪክ የሚጀምርባቸው ዋሻዎች ኃብትን፣ እውቀትንና ታሪክን በውስጣቸው የያዙ የምስጢር ቋቶች ናቸው፡፡
በምስራቅ ሐረርጌ፣ ምዕራብ ባሌ እና አርሲ አካባቢዎች በርካታ አስደናቂ ዋሻዎች በብዛት ይገኛሉ።
ከእነዚህ ዋሻዎች መካከል ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጎበኘው በምስራቅ ሐረርጌ ዞን መልካ በሎ ወረዳ የሚገኘው ናሲኦል ዋሻ ይጠቀሳል።
ይህን ዋሻ ያገኙት፣ መርምረው ርዝመቱን የደረሱበትና በውስጡ ተጉዘው ውበቱን በመቅረጽ ለዋሻ አፍቃሪዎች ያስተዋወቁት የዋሻ ተመራማሪ የሆኑት አቶ ናስር አሕመድ ናቸው፡፡
የዋሻው ስያሜም ከተመራማሪው ስም በመነሳት የተሰጠ ነው፤ “ናሲኦል” የሚለው ስያሜ ከሁሉም የላቀ የሚል ትርጓሜ አለው።
በዋሻው ውስጥ ከ500 ሜትር በላይ በመጓዝ የናሲኦልን ውበት በመመልከት በተፈጥሮ መደነቅ ይቻላል።
ዋሻዎች ካላቸው ባህርይ አንጻር የሕክምና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ፊዚዮቴራፒ እና የቱሪዝም ዋሻዎች በሚል እንደሚከፋፈሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
በዚህ ረገድ በውበቱ እጅግ አስደናቂ የሆነው ናሲኦል ከቱሪዝም ዋሻዎች ጎራ የሚመደብ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡
በቅርብ ጊዜ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የሀገሪቱን የቱሪስት መዳረሻዎች እየጎበኙ ሲሆን፤ ይህንን ድንቅ ዋሻ እንዲጎበኙ በስፋት መስራት ያስፈልጋል።