የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያን ከቀይ ባህር ያራቃት ታሪካዊ ስህተት …

By Hailemaryam Tegegn

March 10, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያን ከቀይ ባህር ያራቃትን ታሪካዊ ስህተት ለማስተካከል በጋራ መስራት ይገባል አሉ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁራን፡፡

በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የባለብዙ ወገን ጉዳዮች ተመራማሪ አዲስ አለማሁ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ ኢትዮጵያ ደካማ እንድትሆን የሚፈልጉ ኃይሎች ባደረጉት ጫና የነበራትን የባህር በር አጥታለች።

ኢትዮጵያን ከአሰብ እና ቀይ ባህር ነጥሎ ማየት አይቻልም ያሉት ተመራማሪው÷ ሀገሪቱን ከባህር ያራቃትን ታሪካዊ ስህተት ለማስተካከል በጋራ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡

መንግሥት የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ በማንሳት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲገነዘበው የሚያደርገው ዲፕሎማሲ ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው÷ በጋራ ተጠቃሚነት እና በሰጥቶ መቀበል መርህ ጥያቄው ምላሽ እንደሚያገኝ ጠቅሰዋል።

ለዚህ ደግሞ ብሔራዊ ጥቅምን መሰረት ያደረገ የተቀናጀ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና ተመራማሪ ሙሉዓለም ኃይለማርያም በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ የነበራትን የባህር በር ያጣችበት መንገድ በዓለም አቀፍ ሕግ ተቀባይነት እንደሌለው አስረድተዋል፡፡

ኤርትራ እንድትገነጠል የወሰነው የወቅቱ የሽግግር መንግሥት ሙሉ በሙሉ በሕዝብ ይሁንታ መንግሥትነትን ያላገኘ እንደነበር አስታውሰው፤ የወቅቱ መንግሥት እንዲህ ዓይነት የሉዓላዊነት ውሳኔ የመወሰን አቅም እንዳልነበረው ተናግረዋል።

በመሆኑም ውሳኔው ህጋዊ አለመሆኑን ጠቅሰው፤ አሁን ላይ መንግሥት ያነሳው የባህር በር ጥያቄ ተገቢ እና ትክክለኛ ነው ብለዋል።

ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ የተቀናጀ የዲፕሎማሲ ጥረት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተው፤ የኢትዮጵያን እውነት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስረዳት ይገባል ነው ያሉት።

በሚኪያስ አየለ